የኢትዮጵያ ካራቴ ውድድር በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሯል

77
ድሬዳዋ ሰኔ 11/2010 የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ዛሬ በድሬዳዋ ተጀመረ፡፡ ውድድሩ ብቃታቸውን የሚያሳዩበትና የርስ በርስ ግንኙነታቸው የሚያጠናክሩበት አጋጣሚ እንደሚፈጥላቸው ስፖርተኞች ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካራቴ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኢትዮጵያ በሬቻ በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና አምስት ክልሎች፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ “በስፖርቱ ሀገርን በአለም አደባባይ የሚያስጠሩ ምርጥ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያግዛል” ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሁሉም ክልሎች በስፖርቱ እንዲሳተፉ ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ከድር ጁሃር በበኩላቸው ስፖርቱ ለስብዕና መጎልበት ጥበብ የሚቀሰምበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ስፖርተኞችም ስፖርታዊ ጨዋታነትን በመላበስ ውድድሩን እንዲያካሂዱና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል፡፡ በውድድሩ ከትግራይ፣ ከአፋር፣ ከደቡብ፣ ከቤንሻጉል፣ ከሐረሪ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ የተውጣጡ 170 ስፖርተኞች፣ አሰልኞችና የቡድን መሪዎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ የካራቴ ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማትያስ አስራት በሰጡት አስተያየት ውድድሩ ወጣቶች ስብዕናቸውንና ጤናቸውን በመጠበቅ ያላቸውን በጎ ነገሮች የሚጋሩበት ነው፡፡ ''ከሁሉም ክልሎች ከመጡ አቻዎች ጋር ልምድ ለመቅሰምና አፋርንም ይበልጥ ለማሳወቅ ያግዛል'' ያለው ደግሞ የአፋር ክልልን የወከለው ስፖርተኛ ጌታቸው ሞላ ነው፡፡ ክልሉ ለስፖርቱ መጎልበት በታዳጊዎች ላይ በመስራት የተሻሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት የበለጠ መስራት እንዳለበትም ጠቁሟል፡፡ ከቤንሻጉል ጉሙዝ የመጣችው ፈቲሃ አክሊሉ በበኩሏ ለክልሉ ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ለማምጣት መዘጋጀቷን ገልጻ በቀጣይ ባላት ብቃት ሀገሯን ወክላ በአለም አደባባይ ስንደቋን ከፍ የማድረግ አላማ እንዳላት ተናግራለች፡፡ የድሬዳዋ ስፖርተኛው አንተነህ አለማየሁ ወደ ድሬ ለመጡት ስፖርተኞች የድሬዳዋን የፍቅር፣ የመተጋገዝ የመቻቻልና የህብረት እሴቶች ለማስረዳት አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ገልጿል፡፡ በውድድሩም ድሬዳዋን አጠቃላይ አሸነፊ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁሟል፡፡ የውድድሩ ተካፋዮች ዛሬ ዕጣ ያወጡ ሲሆን በወንድና በሴት ዘርፎች የነጠላና የቡድን ውድድራቸውን ማምሻውን ማካሄድ ይጀምራሉ፡፡ በወጣው እጣ መሰረት በሴት ነጠላ ካታ ትግራይ ከቤንሻጉል፣ አዲስ አበባ ከድሬዳዋ፣ በቡድን ደግሞ ትግራይ ከቤንሻንጉል፣ አዲስ አበባ ከድሬዳዋ ይወዳደራሉ፡፡ በወንዶች ነጠላ ካታ ድሬዳዋ ከአዲስ አበባ፣ ቤንሻንጉል ከደቡብ፣ ትግራይ ከሐረሪ ሲወዳደሩ በቡድን ደግሞ ሐረሪ ከድሬዳዋ፣ ትግራይ ከቤንሻጉል ውድድራቸውን ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም