የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የእርስ በእርስ መገማገሚያ መድረክ የሠላም ኖቬል ላሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደስታውን ገለፀ

74
ጥቅምት 6/2012 የአፍሪካ አገራት ታዋቂ ሰዎችንና ምሁራንን ያሰባሰበው 'የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የእርስ በእርስ መገማገሚያ መድረክ' የ2019 የሰላም ኖቬል ሽልማት ለተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት አስተላለፈ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዝሃትን በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፤ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ምህዳርን በማስፋት፣ በጾታ እኩልነት እንዲሁም በሃሳብ ነጻነትና ዕርቅ ዙሪያ በአፍሪካ ቀንድ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወናቸውን መድረኩ አስታውሷል። ሽልማቱም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰላምና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ለማጠናከር ላከናወኑት ተግባር የተሰጠ ነው ብሏል። በግጭት ምክንያት ለሁለት አስርታት የተቋረጠውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በመፍታት ሰላም ማስፈናቸውንም አውስቷል። ይህ ታሪካዊ ክስተት በኢትዮጵያ ብሎም በመላው አፍሪካ ሰላምን በማስፈን አህጉሪቱን በአውሮፓዊያኑ 2020 ከጦር መሳሪያ ነፃ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ስንቅ ይሆናል ሲልም መድረኩ አመልክቷል። በአፍሪካ ሰላምን ማረጋገጥ በአህጉሪቱ ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ የተያዘውን የ2063 የልማት ውስጥ ከግብ ለማስረስም ያግዛል ብሏል። በአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ2003 የተቋቋመው የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የእርስ በእርስ መገማገሚያ መድረክ በአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ፈቃደኝነት የተመሰረተና በሁለንተናዊ ጉዳዮችን ራስን በራስ በመገምገም አህጉራዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነው። የግምግማ መድረኩ በአፍሪካ አገራት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ የመንግስታት አስተዳድራዊ እሴቶች፣ ደንብና ስርዓት ረገድ ወጥነት እንዲኖራቸውም ይሰራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም