የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ለማልማት እየተሰራ ነው

92

ጥቅምት 6/2012  የዘንድሮው የአለም የቱሪዝም ቀን በኢሉአባቦር ዞን በዲዱ ወረዳ ተከብሯል::

በበዓሉ ላይ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ሮዛ መሐመድ እንደገለፁት በዞኑ ከእምቅ ሀብትነት ባለፈ እስከ አሁን ጥቅም ላይ ያልዋሉ መስህቦችን በማልማት ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ህብረተሰቡንና የመንግስት ተቋማትን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ ነው::

በዩኒስኮ በአለም ቅርስነት የተመዘገበውን የያዮ የተፈጥሮ ደን እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ከጢስ አባይ ቀጥሎ ትልቁ የሆነውን የሶር ወንዝ ፏፏቴን ጨምሮ ሰባት የዞኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በክልሉ የቱሪዝም ካርታ በማካተት የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል::

በዞኑ ለኢኮኖሚ ልማቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው የሚችል በርካታ ቅርሶች ቢኖሩም ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ባለመልማታቸው በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ሳይሰጡ ቆይተዋል::

በመስኩ ከተለዩት ችግሮች መካከል የሴክተር መስርያ ቤቶች ትኩረት ማነስ በጠቀሜታው ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና የባለሀብቱ ተሳትፎ ውሱንነት በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው::

ሀላፊዋ እንዳሉት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የቱሪዝም ማዕከላትን በማቋቋም የሴክተር መስርያ ቤቶችንና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ካለፈው አመት ጀምሮ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል::

በዞን ደረጃ የቱሪዝም ሀብቶችን በማሰባሰብ ለማስተዋወቅ ለሚገነባው የቱሪዝም ማዕከልም በመቱ ዩኒቨርስቲ ድጋፍ የዲዛይን ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል::

የኢሉአባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ከበደ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ለልማት ለማዋል አስተዳደሩ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው::

የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ጉባኤ አባል አባ ገዳ ተሰማ ሙሉነህ እንዳሉት ደግሞ የቱሪዝም ሀብቶችን መጠበቅ መንከባከብና ማስተዋወቅ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባሻገር ለሀገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ስላለው ህብረተሰቡ በንቃት ሊሳተፍ ይገባል::

በዞኑ ዲዱ ወረዳ በተከበረው በዓል ላይ የዞኑ የቱሪዝም ሀብቶችንና የባህል ምግቦችን የሚያሳይ ኤግዝብሽን ተካሔዷል ።

ከዞኑ 11 ወረዳዎች የተወጣጡ የባህል ቡድን አባላት፣ አባገዳዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተሳትፈውበታል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም