የፊንላንዱ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የአካቶ ትምህርት ዘርፍ እየተከናወነ ያለውን ስራ አደነቁ

99
ኢዜአ፤ጥቅምት 5/2012 የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ በኢትዮጵያ በአካቶ ትምህርት ዘርፍ እየተከናወነ ባለው ስራ መደሰታቸውን ተናገሩ። በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የሐምሌ 1967 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎብኝተዋል። ፊንላንድ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ቤቱ የአካቶ ትምህርት ስርዓትን ለማጠናከር የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች። ፕሬዚዳንቱ ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት ''ፊንላንድ በየትኛውም ሁኔታ አዲስ ክህሎት ቀስመው ደስተኛ የሆኑ ህጻናትን መመልከቷ ደስታን ይሰጣታል''። በጉብኝታቸው ወቅት በትምህርት ቤቱ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸው ወደ ፊት ለአገር የሚጠቅሙ ታዳጊዎችን ማስተማር የተሻለ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል። የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ፤ ፊንላንድ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል። የትምህርት ዘርፍን ለማጠናከር በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 40 ሺህ ገደማ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም የአካቶ ትምህርት ማዕከላትን በማስፋት በኩል ብዙ ስራ እንደሚቀር ዶክተር ጥላዬ አስረድተዋል። በተለይ ከዘላቂ የልማት ግቦች አኳያ አሁንም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአካል ጉዳተኛ  ህጻናትና ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳልመጡም ገልጸዋል። አካቶ ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች በብዛት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲቀላቀሉ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። የአካቶ ትምህርት በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ላይ በስፋት የተቀመጠና በትኩረት የሚተገበር እንደሆነም አመልክተዋል። የሐምሌ 1967 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ዓለምዬ ደምሴ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ 185 አካቶ ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች እንዳሉ ገልጸዋል። ተማሪዎቹን በአግባቡ ለማስተማር የፊንላንድ መንግስት ከስልጠና ጀምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን በማሟላት በኩል ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። በትምህርት ቤቱ በሚገኙ ተማሪዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይፈጠር መደበኛ ትምህርቱ እየተሰጠ መሆኑንም ርዕሰ መምህሯ ተናግረዋል። በእለቱ ለፕሬዚዳንት ሳውሊ የአገር ባህል ልብስ ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን ከልዑካናቸው ጋር በመሆን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ችግኝ ተክለዋል። የኢትዮጵያና ፊንላንድ ልማታዊ ትብብር የተጀመረው እ.አ.አ በ1967 ሲሆን ፊንላንድ በትምህርት፣ በንጹህ የመጠጥ ውኃና የጤና አጠባበቅ፣ በገጠር ልማትና ሌሎችም መስኮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም