በአማራ ክልል ምርጥ ዘር እንዲመረት በማሳ ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ ማከናወን እንደሚገባ ተጠቆመ

88
ባህርዳር ኢዜአ ጥቅምት 5/2012  በአማራ ክልል የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የምግብ ሰብል ዘር እንዲመረት በማሳ ላይ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ማከናወን እንደሚገባ ተጠቆመ። የክልሉ የዕፅዋት ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራትና ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ደባሱ ዛሬ  በሰጡት መግለጫ በ2011/2012 የምርት ዘመን  በክልሉ ከ11ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ልዩ ልዩ ምርጥ ዘር እየተባዛ ይገኛል። ከሚባዛው የሰብል ዘር ውስጥ  በቆሎ፣ ስንዴ፣ ቢራ ገብስ፣ ጤፍና ጥራጥሬ  እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል። ዘሩ 90 በመቶው በአርሶ አደሮች ማሳ እየተባዛ መሆኑንና  የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲመረት ባለስልጣኑ በመስክ በመገኘት ተደጋጋሚ የማሳ ላይ ቁጥጥር ስራ ማከናወኑን አመልክተዋል። በዚህም በዘር ከተሸፈነው መሬት 724 ሄክታሩ  ርቀቱን አለመጠበቅ፣ የባዕድ ዝርያዎች መቀላቀልና ሌሎች ችግሮች እንደተስተዋሉበት ተለይቷል። ዘር አይሆኑም ተብሎ የተለየው  በቀጣይ ወደዘር እንዳይገባ  ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ቁጥጥርና  ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል። እየተባዛ ያለው ቀሪ ምርጥ ዘር በባለስልጣኑ ባለሙያዎች ባደረጉት ተከታታይ የመስክ ጥራት ቁጥጥር ስራ እስካሁን  ችግር  እንዳልተገኘበት አስረድተዋል። ሳይንሳዊ አሰራሩን ጠብቆ የተባዛ ምርጥ ዘር ምርትን እስከ 50 በመቶ እንደሚያሳድግ በባለሙያዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱም ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የገለጹት። በተለይ የዘር ጥራት ቁጥጥሩን እየተፈታተነ ያለው በዘር አሰባሰብ ወቅት በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት  የተመረተው  ዘር ሳይቀላቀል ጥራት ባለው አውድማ ተወቅቶ በቀጥታ ወደ መጋዘን መግባት ይኖርበታል። "አሁን ፈጥኖ የደረሰው የሰብል ዘር መሰብሰብ የሚጀምሩበት ወቅት በመሆኑም የጥራት ችግር እንዳይከሰት በተዋረድ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት  ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል "ብለዋል። ዘር አባዥ አርሶ አደሮችና ድርጅቶችም የተባዛው ዘር የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተሰብስቦ ጥቅም ላይ እንዲውል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል። ለዘር ጥራት መጓደል ዋነኛ ችግር እየሆነ ያለው ክልሉ ለዘር ብዜት የሚሆን መሬት ተለይቶ ባለመዘጋጀቱ እንደሆነም ጠቅሰው ይህም ክልሉ እስካሁን በዘር ራሱን እንዳይችል እንዳደረገው አመልክተዋል። በክልሉ በምርት ዘመኑ  በተለያየ የሰብል ዘር እየተባዛ ከሚገኘው መሬት  300ሺህ ኩንታል ያህል ምርጥ የዘር ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም