በአማራ ክልል 200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፈነ

71
ባህርዳር ሰኔ 10/2010 በአማራ ክልል እየጣለ ያለውን የክረምት ዝናብ በመጠቀም 200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ቁምላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት  በ2010/2011 የምርት ወቅት  ለማልማት ከታቀደው አራት ሚሊዮን 460 ሺህ ሄክታር መሬት እስካሁን 407 ሺህ ሄክታሩ ታርሷል። በአርሶ አደሩ ታርሶ ከተዘጋጀው ከዚሁ መሬት ውስጥ  206 ሺህ ሄክታሩ በበቆሎ፣ ማሽላ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ድንችና ቀድሞ በሚዘራ ሌላም የሰብል ዘር በመሸፈን እየለማ ይገኛል፡፡ ቀሪውን የእርሻ መሬትም በቀጣይ እንደየዘሩ  ወቅት  በተመሳሳይ የመሸፈን ስራ እንደሚካሄድ  ዳይሬክተሩ አመልክተው፤ አርሶ አደሮቹ የተሻሻሉ አሰራሮችን እንዲተገብሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለመኽር እርሻውም ከሶስት ሚሊዮን 500 ሺህ  ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እስካሁን መቅረቡንና ከዚህም ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጠው ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል። እንዲሁም ከተዘጋጀው  120 ሺህ ኩንታል ከሚጠጋው ምርጥ ዘር ግማሽ ያህሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። የዩሪያ ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ለማሟላትም ከወደብ ወደ ክልሉ የማጓጓዝ ስራ መቀጠሉም ተጠቁሟል። በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጎንባት ቀበሌ  አርሶ አደር ወርቁ እንግዳየ በሰጡት አስተያየት  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መጣል የጀመረውን ዝናብ በመጠቀም ማሳቸውን በበቆሎ ዘር የመሸፈን  ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። በግብርና ባለሙያዎች በበጋ ወቅት ያገኙትን ስልጠና መሰረት አድርገው ያላቸውን ሶስት ሄክታር መሬት በበቆሎ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳና  በርበሬ እንደሚያለሙም ጠቁመዋል፡፡ ጥቅም ላይ የሚውል አምስት ኩንታል ማዳበሪያ መግዛታቸውን ጠቅሰው  የዩሪያ ማዳበሪያ  የአቅርቦት እጥረት እንዳጋጠማቸውም አመልክተዋል። ያላቸውን መሬት በስንዴ ዘር ለመሸፈን መሬቱን እያለሰለሱ  እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የከለልቻ ቀበሌ አርሶ አደር ስሜነህ ሞላልኝ ናቸው፡፡ ለዘር የሚሆን ስንዴና የማዳበሪያ ግብዓትም በወቅቱ መግዛታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የምዕራብ አማራ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ መልሴ እንዳመለከቱት  የዘንድሮው የክረምት ዝናብ መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህም በደቡብ ጎንደር ፎገራና ሊቦከምከም፣ በማዕከላዊ ጎንደር ደግሞ ደንቢያ ወረዳዎች ጎርፍ ሊያጠቃ ስለሚችል ህብረተሰቡ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለይ መደበኛው ዝናብ በምዕራብ አማራ በሚያዚያ ወር አጋማሽ መጣል ይጀምር የነበረው ዘግይቶ ቢገባም ከምዕራብ ጎንደር አካባቢዎች በስተቀር ዝናቡ ለዘር ስራው አመቺ በሆነ መልኩ እየጣለ እንደሚገኝ  አስረድተዋል። በአማራ አካባቢ በምርት ዘመኑ  ከሚለማው መሬት 110 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል። ይህም ባለፈው ዓመት ከተገኘው  በዘጠኝ ሚሊዮን 500ሺህ ኩንታል ብልጫ  እንደሚኖረው ይጠቀበቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም