የአክሱም ቅርሶችን ለመጠገን የሚያስችል ጥናት ተካሄደ

128
አክሱም ሰኔ 10/2010 ጥንታዊውን የአክሱም ቅርሶችን ጥገና ለማድረግ ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየውን ጥናት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ በጥናቱ ለተገኙ ውጤቶች ተጨማሪ ግብአት ለማሰባሰብ  በአክሱም ከተማ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ትናንት በተካሄደበት ወቅት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እንደተገለጸው የጥገና ስራ ለመጀመር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ)  የጥናቱ ግብረ መልስ እየተጠበቀ ነው፡፡ ጥናቱን ያካሄደው የኤም ኤች ኢንጂነሪግ ተወካይ ዶክተር መሰለ ሀይለ እንደገለጹት  ቅርሶቹ በጎርፍና ዝናብ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ “የአክሱም ሀውልት ከማዘመም ጀምሮ ጥንታዊ መካነ መቃብሮችና የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የተካሄደባቸው ቦታዎች  ጎርፍ እየገባባቸው  ለአደጋ መጋለጣቸው በጥናት ተረጋግጧል'' ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የጎርፉ ውሀ ከቅርሱ  የሚወጣበት ስልት ማበጀት እንደሚገባ  ተናግረዋል፡፡ ጥናቱ እስካሁን የቆየበት ምክንያት በክረምትና በጋ  ወቅት ጥናት መደረግ ስለነበረበትና የችግሩ ምንጭ ለመለየት  መሆኑን ዶክተር መሰለ ገልጸዋል፡፡  የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው እንዳሉት ጥናቱ  እስካሁን የዘገየው ከባለሙያዎች ተጨማሪ አስተያየት እና ግብአት እንዲካተትበት ስለተፈልገ ነው፡፡ አሁን ጥናቱ ውጤት በሚያመጣ መልኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ ወደ ትግበራ  ምእራፍ ለማሸጋገር ደግሞ  የዩኔስኮ  ይሁንታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ “በተለይም የአክሱም ሐወልቶች  በዩኔስኮ የተመዘገበ  አለም አቀፍ ቅርሶች በመሆናቸው ከዩኒስኮ ግብረ መልስ መጠበቅ ግድ ይላል'' ብለዋል፡፡ በአውደ ጥናቱ  የከተማው ነዋሪዎችና በቅርስ ጥገና ሙያና ትምህርት ያላቸው ምሁራን ተካፍለዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ  ቅርሶቹ  አሁን ካሉበት ሁኔታ ሲታይ የጥገናው ስራ መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡ ጥገናው  ሲጀመር የቅርሶቹ ታሪካዊ እሴት እና ትውፊት በማይነካ መንገድ መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ግርማ መላኩ በበኩላቸው የቀረበው ጥናት ቅርሶቹን እንደሚታደግ  ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጀመር እና ቅርሶቹ ከስጋት ነጻ ለማድረግ  ባለስልጣኑ መከታተል እና ማስጀመር እንዳለበት አሳስበዋል። ጥናቱ “ኤም ኤች ኢንጅነሪንግ'' በተባለ ሀገር በቀል እና “ስቱዲዮ ክሮቺ'' በተባለ የጣሊያን አማካሪ ድርጅቶች መካሄዱን ተገልጸዋል፡፡ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ከአማካሪ ድርጅቶቹ ለቅርሶቹ ጥገና ጥናት እንዲያደርግ ከባለስልጣኑ  ስምምነት መደረጉን ይታወቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም