"አድዋ ጥንት አባቶቻችንና አያቶቻችን በቃል ኪዳን ተነስተው በደምና በአጥንታቸው እኛ ኢትዮጵያውያን እንዳንለያይ የገመዱበት ነው"... ኢንጂነር ታከለ ኡማ

137
ጥቅምት 4/2012 አድዋ አባቶቻችንና አያቶቻችን በቃል ኪዳን ተነስተው በደምና በአጥንታቸው እኛ ኢትዮጵያውያን እንዳንለያይ አድርገው በትልቅ ሰንሰለት የገመዱበት ነው ሲሉ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ። የአድዋ ፓርክ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርአት ተካሔደ። አስተዳደሩ በራሱ ወጪ ፓርኩን የሚገነባው የአድዋ ጀግኖች አባቶቻችንን ለመዘከር መሆኑም በዚሁ ፕሮግራም ላይ ተጠቁሟል። ምክትል ከንቲባው ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት "ጥንት አባቶቻችንና አያቶቻችን ያኔ መስዋእት ባትከፍሉ ባትተባበሩ እኔና መሰሎቼ በአዲስ አበባ ምድር ቆመን ያባቶችን ገድልና ታሪክ ማውራት አይቻለንም ነበር"። ዛሬ ያለው ትውልድም ለናንተ ያለው ክብር "ዝቅ ብዬ እገልጽላችኋለሁ" እናመሰግናለን። "አድዋ የጋራችን ታሪክ ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባው  "በእኛ በልጆች ልብ ውስጥ ሁል ጊዜ የሚታወስና እንረሳለን ብንል እንኳን መርሳት የማንችል፤ እንለያየለን ብንል እንኳ እንዳንለያይ በብርቱ ሰንሰለት የተገመድንበት ነው"። ''ታሪክ የለንም የጋራ ጉዞ የለንም ብንል እንኳን ሕያው የሆነ አድዋ የሚመሰክርብን ታላቅ ሕዝብ ነን፤ የጋራ ታሪኮቻችን ለልጆች፣ ለአባቶች ለሚቀጥለው ትውልድ ብንችል በጽሑፍ ባንችል ደግሞ እንደ አድዋ ያሉ ማእከላትን በመገንባትና ጽናቶችን በማስቀረት ከዚያ የሚገኙ ውጤቶችን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል''። ምክትል ከንቲባው አክለውም ''የአገራችን ዋና ከተማ  የብሔሮች ብሔረሰቦች መኖሪያ አዲስ አበባችን፤ ሁሉም ነገር ከዚህ እንደሚጀምርና ምንጩ ከዚህ እንደሆን የሁሉም ዜጎች የታሪካቸው፣ የኢኮኖሚያቸውና የማሕበራዊ ህይወታቸው ውሳኔ ምንጩ ከዚህ እንደሆነ እንዲያውቁ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ተብሏል'' ነው ያሉት። የጋራ ታሪኮቻችን አንድነታችንን ስለሚያጠናክሩ እንከባከባቸዋለን ያሉት ኢንጂነር ታከለ፤ ታሪኮቻችን የእኛ የጉዞ አካል ናቸው፤ ማናችንም ታሪክን መሻር አንችልም፤  ማናችንም ብንሆን ታሪክ ከመስራትና ከማደስ ውጭ የተሰራውን ታሪክ መሻር አንችልም ሲሉም አመልክተዋል። ዶክተር ዳኛቸው አሰፋም "ዛሬ ያለው ትውልድ ያለው አማራጭ እንደ አባቶቻችን ከልዩነቶች ይልቅ አንድነትን፤ ከመጠላለፍ ይልቅ እንደገና ቃልኪዳን አስረን ሃገራችንንና ልጆቹዋን አሁን በጀመርነው ልክ ወደ ብልጽግናና ወደ ገናና ታሪክ ማማ መውሰድ ነው" ብለዋል። በፕሮግራሙ ላይ  የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞት ማሕበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ እንዳሉትም "አድዋ በቀላሉ የተገኝ ድል አይደለም፤  ከመላው ሀገሪቷ ለአንዲት ኢትዮጵያ ለአንድ ሰንደቅ አላማ የተከፈለ መስዋእትነት ነው" ብለዋል። በዚህ ጦርነት ውስጥ ከተካፈሉት ከግማሽ በላይ የሆነው ሕዝብ በቋንቋ አይገናኝም ነበር፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ በአንድነት ነው የተመመው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም