በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ፈጠራ ሥራን የሚያበረታታ የሶስት ዓመት መርኃ ግብር ይፋ ተደረገ

62
ጥቅምት 4/2012 የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ፈጠራ ሥራን ለማበረታታት የሚያስችል የሦስት ዓመት መርኃ ግብር ይፋ አደረገ። በስምንት ሚሊዮን ዩሮ የሚካሄደው ይኸው መርኃ ግብር በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብና አፋር ክልሎች በሚገኙ 41 ወረዳዎች ላይ ያተኩራል ተብሏል። መርኃ ግብሩ በማኅበራዊ ፈጠራ የሚሰሩ አካላትን ለማስተሳሰርና በዘርፉ ብሔራዊ መልሶ የመቋቋም አቅም ግንባታን ለማጠናከር ይረዳል ነው የተባለው። በመርኃ ግብሩ የሚለቀቀው የገንዘብ ድጋፍም የ20 ሺህ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በቀጥታ ለመለወጥ የሚያስችል የፈጠራ ሥራን የሚያበረታታ መሆኑ ተጠቅሷል። በመርኃ ግብሩ ተጠቃሚ ከሚሆኑት መካከል 50 በመቶው ሴቶች እንደሚሆኑም ተገልጿል። በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መርኃ ግብሩ የማኅበራዊ ፈጠራ ለአገሪቱ ልማት ያለውን አስተዋጽጾ በተመለከተ ግንዛቤ የማስጨበት ሥራም ይሰራል። የማኅበራዊ ፈጠራ ትኩረት የሚሰጠው የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆንና የዘርፉን የቴክኖሎጂ ሽግግር ማሳለጥም ሌላኛው የመርኃ ግብሩ ዓላማ ነው። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ የመርኃ ግብሩ አስተባበሪ ኢማ ጉዩሴ በአሁኑ ወቅት የማኀበራዊ ፈጠራ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በዓለም አቀፍም ይሁን በአገር ደረጃ የተለያዩ አዳዲስ ማኅበራዊ ችግሮች እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸው ለዚህም መፍትሄ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ይህ አይነቱን መፍትሄ ለማምጣት የማኀበራዊ ፈጠራን እያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። በመርኃ ግብሩ ድጋፍ የተደረገላቸው ግለሰቦችና ተቋማት የፈጠራ ሥራቸው ስኬታማ ከሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናደረጋለንም ነው ያሉት። ተቋማዊ ቁመና እንዲኖረው እና በመርህ እንዲመራም ለማድረግ የአውሮፓ ኅብረት ጥረት እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ እንዳሉት የፈጠራ ሥራን ለማበረታታትና ምቹ ማዕቀፍ ለመፍጠር ሚኒስቴሩ እየሰራ ነው። በቴክኖሎጂ ዘርፍ አዳዲስ ፈጠራዎችን ላማስፋፋት ፈንድ የማቅረብና የቴክኖሎጂ የልዕቀት ማዕከል ማስፋት ላይ ትኩረት ማድረጉንም ተናግረዋል። በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው መርኃ ግብርም መንግሥት የያዛቸውን ሥራዎች በማጠናከርና ዘርፉን በማጎልበት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። መርኃ ግብሩን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ በአምስቱም ክልሎች የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት መለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። የመርኃ ግብሩ የገንዘብ ድጋፉ የተገኘው ከአውሮፓ ኅብረት የመተማመኛ ፈንድ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም