የበለጸገች አገርን እውን ለማድረግ ጤንነቱ የተረጋገጠ ማህበረሰብን መፍጠር ይጠይቃል - ኢንጂነር ታከለ ኡማ

123
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 4 ቀን 2012 የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠት ትውልዱን በመልካም ስነ-ምግባርና እውቀት ከመገንባት ባሻገር ጤንነቱም በአስተማማኝ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ። 21ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል። የከተማው ምክትል ከንቲባ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለስልጣናትንና ሙያተኛውን ጨምሮ መላው ዜጋ የድርሻቸውን መወጣት ሲችሉ ነው የአገር ብልጽግና  የሚረጋገጠው። በመሆኑም የበለጸገች አገር ለመፍጠት ትውልዱን በመልካም ስነ-ምግባርና እውቀት ከመገንባት ባሻገር ጤንነቱም በአስተማማኝ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በየትኛውም የሙያ መስክ የተሰማሩ ዜጎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለአገሪቱ እድገት ምክንያት መሆን አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል። የተማረና ጤናማ ዜጋ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልጽግና ወደ ከፍታ ማማ ለማድረስ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግልም ገልጸዋል። የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው፤ አገሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የጀመረችው ጥረት ይሰምር ዘንድ ጤናማ ማህበረሰብን መፍጠር ይጠበቅባታል ብለዋል። በዚህም መሰረት መንግስት የዜጎችን ጤና ለማሻሻል በትጋት እየሰራ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል። መንግስት የጤናው ዘርፍ የሚመራበትን የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረፅ እስካሁን ባከናወነው ተግባርም የዜጎች ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ማሳደግ መቻሉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል። እንደ ጤና ሚኒስትሩ ገለጻ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትና ጥራት ችግር፣ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል መልኩ አለመተግበር፣ የጤና አገልግሎት ግብኣት እጥረት በዘርፉ ያሉ ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው። በዚህም የተነሳ በተለይም በክትባትና የስነ-ምግብ አገልግሎት፣ በስነ አእምሮ ጤና፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መከላከል፣ በየጨቅላ ህጻናት ጤንነትና የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ብለዋል። እነዚህን ችግሮች በመፍታት የዘርፉን የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት በተያዘው በጀት ዓመት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። 21ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔው “ዘርፈ ብዙ ትብብር ለጤናማና የበለጸገች አገር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። በጉባኤው ላይ ከመላው ኢትዮጵያ የተጋበዙ የጤናው ዘርፍ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች ማህበራት እየተሳተፉ ነው። ለሚቀጥሉት አራት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው ዘርፉ ባስቀመጣቸው የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አተገባበር፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ይመክራል። በጉባዔው በጤናው ዘርፍ ለተመዘገቡት ውጤቶች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና በዘርፉ ለተሰማሩ ጤና ሙያተኞችና ተቋማት ሽልማት ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም