ሞዴል ኢንተርፕራይዞችንና ስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

106
አዲስ አበባ ሰኔ 10/2010 ሞዴል ኢንተርፕራይዞችንና ስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት ከተሰራው ያልተሰራው ስለሚበልጥ የጋራ ጥረትና ርብርብ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። በበጀት አመቱ በዘርፉ በአገር አቀፍ ደረጃ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ የዘርፉ አስፈጻሚ ተቋማትና ባለሙያዎች የዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በስነ ስርዓቱ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደገለጹት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሞዴል ኢንተርፕራይዞችንና ስራ ፈጣሪዎችን ማፍራት፣ መደገፍና መንከባከብ ያስፈልጋል። “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራት 'ከሰራነው ያልሰራነው' ይበልጣልና ከዚህ በላይ ውጤት ለማምጣት ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል" ብለዋል። ዕውቅና የተሰጣቸው ሞዴል ኢንተርፕራይዞች፣ የዘርፉ አስፈጻሚ ተቋማትና ባለሙያዎች በትጋት ሰርቶ ድህንነትን ለማንበርከክ እንደሚቻል በተጨባጭ ካረጋገጡት ውስጥ ነጥረው የወጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ በዓመቱ የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ 300 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች፣ ወደ ታዳጊ መካከለኛ የተሸጋገሩ 100 ኢንተርፕራይዞች፣ 108 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችና ባለሙያዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። 11 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት እንዲሁም 11 አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ለዘርፉ አመታዊ የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ዘጠኝ የከተሞች የምግብ ዋስትና ተቋማት ሞዴል ሆነው መውጣት በመቻላቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ሁለት የታዳጊ ክልሎች የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ ተቋማት የላቀ ተሞክሮ ያስመዘገቡ በመሆኑ ዕውቅና አግኝተዋል። በዘርፉ ተሰማርተው ሞዴል ለመሆን የበቁ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ ምሩቃንና የስደት ተመላሾችን ያሳተፈ ነው። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩላቸው 'ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ያለንን ጉልበት እውቀትና ጊዜ ሳንሰስት በተደራጀ መንገድ በመረባረብ ለውጥ እንድናስመዘግብ ግድ የሚለን ወቅት ነው' ብለዋል። "እምቅ ጉልበትና ሀይል ያለውን ሕብረተሰብ ወደ ስራ ልናሰማራ የምንችልባቸውን መንገዶች መፈተሽ፣ ከሕብረተሰቡ ጋር በየጊዜው መወያያትና ከጎናችን እንዲቆም ማድረግ የቤት ስራችን እንደሆነ እናምናለን" ብለዋል። ለወጣቶች ከተመደበው 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ውስጥ 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች መሰራጨቱ ታውቋል። ለከተሞች ከተያዘው ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ውስጥ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር የተሰራጨ ሲሆን ከተጠቃሚዎቹ ውስጥም 37 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ የኢንተርፕራይዞች ሽግግር እንዲመዘገብ የዕድገት ደረጃቸውን መሰረት ያደረገ የድጋፍ ማዕቀፍ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደስራ ከገባበት ጀምሮ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች በተመረጡ የስራ መስኮች የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ዘርፉ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት ፈተና ሆኖበታል። የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተመረጡ 11 ከተሞች ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ  ነው። በመርሃ ግብሩ 440 ሺህ 885 ዜጎችን በአካባቢ ልማትና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም