በአፋር ክልል ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ታቅዳል

84
ሰመራ ኢዜአ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በአፋር ክልል በመጪዎቹ 5 ዓመታት ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም አሰፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ። በአፋር ክልል ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የወጣ ብሄራዊ ፍኖተ-ካርታ ለማስተዋወቅ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ትናንት በሰመራ ከተማ ተካሄሔዷል ። በመድረኩ ላይ የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋየ እንደተናሩት ባለፉት ተከታታይ አመታት በክልሉ ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ አስተምህሮና የመከላከልና ስራዎች ተከናውነዋል ። በዚህም ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ በክልሉ ይከናወኑ የነበሩት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መሻሻል አሳይተዋል ሆኖም ግን ከሚፈለገው ውጤት አንጻር የተገኘው ውጤት አጥጋቢ ባለመሆኑ ለተሻለ ውጤት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ። በመሆኑም ሀገራችን በ2017 በሀገሪቱ የሚፈጸሙ የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለእድሜ ጋብቻን ሙለሙሉ ለማስቆም የገባችውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ የ5 ዓመት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ። በፍኖተ-ካርታው መሰረት በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛትና ያለእድሜ ጋብቻ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ላይ አስፈላጊውን በጀትና ግብአት በማሟላትና ተያያዥ ድጋፎችን በማድረግ ተጠያቂነት ያለው የተቀናጀ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል ። የአፋር ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን እንዳሉት ደግሞ  በክልሉ የሚፈጸመው የሴት ልጅ ግርዛት በሴቶች ስነ-ተዋልዶ ጤናና የስነ-ልቦና ችግር የሚያስከትል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው ። ይህን ችግር ለመቅረፍ ባለፉት አመታት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሰፊ የአስተምህሮና የመከላከል ስራዎች ቢከናወኑም አሁንም 90 በመቶ የሚሆኑ የአፋር ሴቶች የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል ። ችግሩን ለመግታትና ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ከአመራሩ ጀምሮ የጉዳዩ ባለቤትና ዋነኛ ሰለባዎች የሆኑት ሴቶች በቁርጠኝነት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል ። የአፋር ክልል የአስልምና ጉዳይ ተወካይ ሼክ ሀይደራ አሊ በበኩላቸው እስከ አሁን በአብዘኛው የተሰሩ የፀረ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የአስተምህሮ ስራዎች በክልሉ ከተሞችና በወረዳ ማእከላት ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው  ችግሩ በብዛት በሚታይበት በገጠር ቀበሌዎች አካባቢ ውጤት እንዳይመጣ አድርጎታል ብለዋል ። በመሆኑም በቀጣይ የሚከናወኑ የአስተምህሮ ስራዎች ዋኛው የችግሩ ማእከል ወደ ሆነው የገጠሩ ክፍል መውረድ እንዳለበት አሳስበዋል ። በውይይት መድረኩ ላይ የወረዳ ሴቶች ጉዳይ ሃላፊዎች፣  የሃይማኖት አባቶችና የፍትህ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም