በታርጫ ከተማ ይካሄዳል የተባለው የመንገድ ግንባታ ባለመጀመሩ ቅሬታ ፈጥሯል

690
ጅማ ሰኔ 10/2010 በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በተያዘው  ዓመት ይካሄዳል የተባለው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ባለመጀመሩ በከተማው አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ። ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብረሃም አሸንጎ እንዳሉት ዘንድሮ  በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ይካሄዳል ተብሎ እስካሁን አልተጀመረም። መንገዱ ያልፍባቸዋል ተብለው  የእሳቸውን ጨምሮ የተለያዩ  ቤቶች ፈርሰው ለመንገዱ ልማት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርም ግንባታው ባለመጀመሩ ቅሬታ አሳድሮባቸዋል። " የፈረሱት  መኖሪያ ቤቶቻችንን በአዲስ መልክ ለመስራት የግድ የመንገዱን መሰራት ጠብቁ ስለተባልን እየተጉላላን ነው" ብለዋል። ሌላዋ ከተማው ነዋሪ ወይዘሪት ትግስት አሰፋ  ለመንገድ ልማት ተብሎ ቤቶች ፈርሰው መቆየታቸው የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸቱም ሌላ የታክሲ ትራንስፖርት ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል። ለመንገዱ ግንባታ እሳቸውና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ገንዘብ በማዋጣት ቢሳተፍም የስራው አለመጀመር ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት ደግሞ አቶ ተስፋዬ አቢጢ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ የታርጫ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ አንበሴ ኡርኩ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የመንገዱ ግንባታ ሊዘገይ የቻለው ለስራው የሚያስፈልጉ ማሽኖች በወቅቱ ተገዝተው ባለመቅውረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት  አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ስድስት የመንገድ ስራ ማሽኖችን ለመግዛት ቢታቀደም ከአቅራቢ ድርጅቱ በቅደመ ከፍያ ግዥ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ የመንገዱ ግንባታ ሳይጀመር ዘግይቷልል። በአሁኑ ወቅት በ5 ሚሊዮን ብር አንድ ግረደር  ተገዝቶ ግንባታው መጀመሩን ከንቲባው ጠቅሰው ተጨማሪ ዶዘር በ11 ሚሊዮን ብር ግዥ ለመፈጸም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በከተማዋ 18 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ስራ ለማከናወን ስድስት ሚሊዮን 700ሺህ ብር ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል። የመንገድ ስራውም እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ  ጥረት እንደሚደረግ ከንቲባው አመልክተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም