በሰቲት ሁመራ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ጾታዊ ጥቃት እየጨመረ ነው

112
ሁመራ ኢዜአ ጥቅምት 4/2012  በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በሰቲት ሁመራ ከተማ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ፆታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡ ጥቃቱን ለመከላከል "የሴቶች ጥቃት የሁሉም ህብረተሰብ ጥቃት ነው " በሚል መሪ ቃል በሁመራ ከተማ የውይይት መድረክ ትናንት ተካሄዷል ፡፡ የከተማው ፍትህ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋይ ስለሺ በምክክር መድረኩ እንደገለጹት በከተማው ባለፈው መስከረም ወር ብቻ  ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆኑ ሶስት ሴት ህፃናት ተደፍረዋል ። ባለፉት ሶስት ወራት የወንጀል ክስ ክስ ከተመሰረተባቸው 220 መዛግብት ውስጥ 45ቱ መዛግብት በሴቶች ላይ የደረሰ ጾታዊ ጥቃት የተመለከቱ ናቸው ብለዋል ። በተጠናቀቀው የበጀት አመትም ቢሆን በአቃቤ ህግ ከተያዙ 270 መዛግብት ውስጥ 134 በሴቶች ላይ የተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው ። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 76 ሰዎች ከ 8 አመት እስከ 12 አመት የፍርድ ውሳኔ ቢሰጣቸውም ወንጀሉ ከመቀነስ ይልቅ አሁንም የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ነው ብለዋል፡፡ የምክክር መድረኩ ዓላማም በከተማው እያጋጠመ ያለውን ተደጋጋሚ የሴቶች ፆታዊ ጥቃት በጋራ በመሆን መፍትሄ ለማምጣት መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡ በተለይም በቅርብ ጊዜ ህጸናት ሴት ልጅ ላይ የታየውን ጥቃት በጣም አስነዋሪና አስደንጋጭ መሆኑን ተገልጸዋል፡፡ የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪ ሸህ ሃሰን በርሄ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት እኛ የሃይማኖት አባቶች ይህንን አይነቱ አስፀያፊ ድርጊቶች ማውገዝ ይገባናል ብለዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በተናጠል ሳይሆን በተደረጀ መንገድ መከላከል ይገባናል ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ  ጥሩነሽ ሲሳይ ናቸው፡፡ ሳጅን ሃይላይ ግደይ በበኩላቸው  በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት በማድረስ  ተጠርጥረው በፖሊስ ከተያዙ በኋላ ከወንጀሉ ነጻ እንዲሆኑ ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ሴቶች በድርድር ተመልሰው ተባባሪ የመሆን አዝማሚያ እንደሚታይ ተናግረዋል ። ድርድሩ ወንጀሉን ከመቀነስ ይልቅ እንዲጨምር እያደረገው መሆኑንም ሳጅን ሃይላይ ገልፀዋል ። የዞኑ ሴቶች ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የኔነሽ ስለሺ በበኩላቸው በዞኑ በተለያየ ጊዜ የሴቶች ጥቃት የሚፈፀም ቢሆንም በኡኑ ጊዜ እየታየ ያለው ግን ከመቼውም የባሰ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም በቅርቡ በሰቲት ሁመራ ከተማ ለአቅመ ሄወን ባልደረሱ ህጸናት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት  የህብረተሰቡን ልብ የሰበረ ነው ብለውታል ።   በሴቶች እየተፈጸመ ያለውን አስነዋሪ ድርጊት ለማስቆም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተቀናጅቶ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል ። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ለማስቆም ለፍርድ-ቤት ወይም ለፖሊስ ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብረመድህን ዮሀንስ ናቸው፡፡ የሴቶች ጥቃት ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት እራሳቸው ሴቶች ተደራጅተው መታገል እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም