የመቱ ዩኒቨርስቲው ለምቹና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስኬት የህብረተሰቡ ድጋፍ ጠየቀ

75
ጥቅምት 4/2012 መቱ ኢዜአ  የመቱ ዩኒቨርስቲ ምቹና ሰላማዊ የትምህርት አካባቢ በመፍጠር የቆመለትን አላማ እንዲያሳካ የአካባቢው ህብረተሰብ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ ጠየቁ:: `` ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ሚና ” በሚል ርእስ ዩኒቨርስቲው  ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ትናንት ውይይት አካሔዷል ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ እንዳሉት ሰላማዊ የትምህርት አካባቢ በመፍጠር በትምህርት: በማህበረሰብ አገልግሎትና በጥናትና ምርምር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል:: ባለፉት ሶስት አመታት በነበረው አለመረጋጋት የተነሳ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ተግባራት ያለመከናወናቸውን ገልፀው ይህንንም ለማካካስ በሚደረገው ጥረት መምህራን ፣ተማሪዎች ፣የአካባቢው ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል:: ዩኒቨርስቲው ለ 10 አመት የሚቆይ የእንስሳት ልማት ፕሮጄክትን ጨምሮ የአካባቢውን ተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋልና ግብርናውን ለማዘመን እቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል:: በተለይም ቅመማ ቅመምን ጨምሮ በአካባቢው የሚለሙና ገበያ ላይ ይበልጥ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በማልማት አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ዩኒቨርስቲው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል:: ዩኒቨርሲቲው እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራትና የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ማህበረሰቡ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱን መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ። የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ጉዳይና አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ተካልኝ ቀጄላ ባቀረቡት ፅሑፍ እንደጠቀሱት ባለፉት ሶስት አመታት በሀገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙለትን የማስተማር ፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የጥናትና ምርምር ተግባራት በሚፈለገው መጠን እንዳያሳኩ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል:: በ2012 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ አንድነትን: መከባበርንና መቻቻልን በማስፈን የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ ትስስር እንዲኖር የበኩሉን የሚወጣ ትውልድ ለመፍጠር ሊሰራ ይገባል ብለዋል:: የመቱ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ፋከልቲ መምህር አቶ ፀጋዬ በርኬሳ በበኩላቸው  ዩኒቨርስቲው በመማር ማስተማሩ ረገድ ውጤታማ እንዲሆን በዋናነት ተማሪዎች ዓላማቸውን አውቀው በትኩረት ትምህርታቸውን መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል ። መምህራንና የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብም  በአግባቡ ተማሪዎቹን በመደገፍ የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል ። የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻፊ ሁሴን እንዳሉት ደግሞ ዩኒቨርስቲው በመማር ማስተማርና ማህበረሰብ አገልግሎት መስኮች ላይ ውጤታማ እንዲሆን የዞኑ አስተዳደር ተገቢውን እገዛና ትብብር ያደርጋል ብለዋል :: በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርስቲው ምሁራን እንዲሁም ከኢሉ አባቦርና ከቡኖ በደሌ ዞን የተወጣጡ የአመራር አካላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል::
     
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም