የዳዋ ጨፋ ወረዳ ነዋሪዎች ለንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መጋለጣቸውን ገለጹ

123
ደሴ ጥቅምት 4 / 2012 በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በዳዋ ጨፋ ወረዳ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተመደበላቸው የውሃ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው ለንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መጋለጣቸውን ነዋሪዎች ገለጹ። ፕሮጀክቱ በያዝነው ዓመት እንደሚጠናቀቁ የወረዳው ውሃና ኢነርጂ ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የወረዳው አንዳንድ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በወረዳው ላለፉት አራት ዓመታት የተጀመረው ፕሮጀክት እስካሁን ባለመጠናቀቁ ንጽህና የተጠበቀ ውሃ ለማግኘት አልቻሉም። በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት ባለመጠናቀቁ ከውሃ እጥረትና ከውሃ ወለድ በሽታዎች ችግሮች አለመለቀቃቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል። የዶዶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሐመድ ከድር የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት  የተጀመረው ፕሮጀክት ባለመጠናቀቁ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንደሚያባክኑ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ''በየዓመቱ 'ዘንድሮ ይጠናቀቃል' እየተባለ ለፖለቲካ ፍጆታ ውሏል'' ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ችግራቸውን ለማቃለል በክረምት ወቅት አጠራቅመው የሚጠቀሙት የዝናብ ውሃ ለውሃ ወለድ በሽታ እያጋለጠን ነው ብለዋል፡፡ በአካባቢያቸው ወንዝም ሆነ ምንጭ አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ገልጸው፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥና በሕዝብ ላይ የሚቀልዱ አመራሮችና ግለሰቦችን ተጠያቂ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ የቢላቻ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሐዲያ ጀማል ከሁለት ሰዓት በላይ ተጉዘው የሚያገኙት ንጽህናው ያልተጠበቀ የወንዝ ውሃ በጤንነታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ወረፋ ለመያዝ "ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ስለምንጓዝ ጉልበታችንና ጊዜያችንን ከማጥፋታችን በተጨማሪ ሴቶች በመሆናችን ለጠለፋና ለመደፈር እየተጋለጥን በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል" ብለዋል፡፡ የዳዋ ጨፋ ወረዳ ውሃና ኢነርጂ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ተስፋዬ ተጠይቀው ፕሮጀክቱ በዲዛይን፣ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ በመንገድ ችግርና በጀት ባለመለቀቁ መዘግየቱን አስታውቀዋል። ግንባታው በአማካይ 94 ነጥብ 5 በመቶ የደረሰው ፕሮጀክት በያዝነው ዓመት ማጠናቀቅ ለአገልግሎት እየተሰራ መሆኑንም  ተናግረዋል። ፕሮጀከቱ ከ20 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ  እንደሚጠበቅና  ከ500 ሜትር ኩብ በላይ ውሃ የሚጠራቅምባቸው ታንከሮች እንደሚገነቡለት ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በወረዳው ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን አሁን ካለበት ከ68  ወደ 78 በመቶ እንደሚያደርሰውም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም