በክልሉ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተያዙ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቀሉ

86
ባህር ዳር ሰኔ 10/2010 በአማራ ክልል በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመወጣት ሲሞክሩ የተያዙ አንድ ሺህ 500 ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ባለሙያ ወይዘሮ የክቴ መንግስቱ ትላንት ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት 11 ወራት  በደላሎች አማካኝነት በመተማና አፋር በኩል ወደ ተለያዩ የውጭ ሃገራት በህገ ወጥ መንገድ ለመውጣት ሲሞክሩ ከተያዙት  መካከል 377ቱ ሴቶች ናቸው። በመውጫ በሮቹ ከተያዙት ውስጥም ከጋምቤላ፣ ከትግራይና ከኢትዮጵያ ሶማሌና ከአማራ ክልሎች የመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር በተደረገ ጥረት የተያዙትን እነዚሁ ዜጎች ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር የትራንስፖርትና የምግብ ወጫቸው ተሸፍኖ ወደየመጡበት አካባቢ ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ህገወጥ ስደትን  ከምንጩ ለማድረቅም ቢሮው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት ከ6 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች ስለህገወጥ ስድት አስከፊነት ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጓል። የሃይማኖት ተቋማትም በየቤተ እምነቶቻቸው የህገ ወጥ ስደትን አስከፊነት ለተከታዮቻቸው እንዲያስተምሩ እየተደረገ ነው። ሆኖም ግን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ወጥ የሆነ ጥናት አለመካሄዱና የህገወጥ ደላሎች የቅስቀሳ ስልት መቀያየር ችግሩን በታሰበው ልክ ማስቆም እንዳላስቻለ ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ወጣቶቹ ተገንዝበው በህገወጥ መንገድ ከሀገር በመውጣት ሊደርስባቸው ከሚችለው ስቃይና መከራ ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባም አሳስበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም