በምስራቅ ወለጋ ዞን ከ200 ሺህ ሔክታር በላይ በዘር ተሸፍኗል

90
ነቀምቴ ሰኔ 10/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን እየተካሄደ ባለው የመኸር እርሻ እንቅስቀሴ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዴ መኮንን  እንዳስታወቁት በዘር የተሸፈነው መሬት በ2010/2011  የምርት ዘመን ለማልማት ከታቀደው 415 ሺህ 614 ሄክታር  ውስጥ ነው። እስካሁን ከተዘሩት ዋና ዋና ሰብሎች ውስጥ በቆሎ፣ ማሽላ ፣ ገብስ፣ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ ዳጉሣና ቅመማ ቅመም ይገኙበታል። በተለይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት በዘር ከተሸፈነው ማሳ ከ50 በመቶ የሚበልጠው ማሳ በሙሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ መልማቱን ተናግረዋል። በአጠቃላይ በመኽር አዝመራው ለማልማት ከታቀደው ውስጥ ከ379 ሺህ ሄክታር የሚበልጥው ታርሶና ለስልሶ ለዘር ተዘጋጅቷል። በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናብ ለእርሻ ስራ አመቺ በመሆኑ አርሶ አደሩ ልማቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ነው አቶ ዘውዴ የገለጹት። ልማቱ በግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳይስተጓጎል ለማድረግም ከ222 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና 34 ሺህ ኩንታል የሚሆን ምርጥ ዘር ቀደም ብሎ ተሰራጭቷል። በዞኑ በዲጋ ወረዳ የአርጆ ጉደቱ የገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ለታ ቱጌ በሰጡት አስተያየት እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም   በአምስት  ሄክታር ማሳቸው ላይ በቆሎ ዘርተዋል። ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር አስፋው ዋቅጅራ በበኩላቸው ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ በመዝነቡ 7 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም በቆሎና ማሽላ በመዝራት እየተንከባከቡ ነው። በምስራቅ ወለጋ በመኽር አዝመራው በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት ከ144 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መካከል ከ16 ሺህ የሚበልጡት ሴቶች ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም