የ2019 የዓለም ምርጥ ወንድ አትሌት እጩዎች ዝርዝር ይፋ ሆነ

117
አዲስ አበባ  ጥቅምት  3 /2012  የ2019 የዓለም ምርጥ ወንድ አትሌት እጩዎች ዝርዝር ይፋ ሲደረግ አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት በዝርዝሩ ውስጥ አልተካተተም። የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የ2019 የዓለም ምርጥ ወንድ አትሌት እጩዎችን ይፋ አድርጓል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ዘንድሮ አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት አለመካተቱ ታውቋል። በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት በአዋቂ ወንዶችና አዋቂ ሴቶች እጩ ዝርዝር ውስጥ አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት አለመካተቱ ይታወቃል። ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በኩል በወንዶች አትሌት ሃይሌ ገብረስለሴ እና ቀነኒሳ በቀለ በሴቶች ደግሞ መሰረት ደፋር፣ ገንዘቤ ዲባባና አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሆነው ተመርጠዋል። ባለፉት ሁሉት ዓመታት ግን ከኢትዮጵያ በአሸናፊነት ቀርቶ በእጩነት እንኳን የተካተተ አትሌት አልተገኘም። ከኬኒያ ባለፈው ዓመት ጥሩ የውድድር ብቃት ነበራቸው በሚል በእጩነት የተካተቱት አትሌቶች አሉ። ማራቶንን ከ2 ሰዓት በፊት የገባው ኬኒያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌና በ1 ሺህ 500 ሜትር ተወዳዳሪ የሆነውና በ2018 -2019 ዳይመንድ ሊግ አሸናፊው ቶሚቲ ቼሮይት ተካተዋል። ኡጋንዳዊው የ5 እና 10 ሺህ ሜትር ሯጭ ጆሽዋ ቼፕቴጌም በእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ተከቷል። አሜሪካ አምስት አትሌቶችን ያስመረጠች ሲሆን በ800 ሜትር የክብረወሰን ባለቤቱ ዶናቫን ብርዜር ፣የአጭር ርቀት ሯጩ ኖህ ሊልየስ በእጩነት ተይዘዋል። በ400 ሜትር ተወዳዳሪው ባህማሳዊው አትሌት ስቴቬን ጋርዲነር በእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ አንዱ መሆን ችሏል። በሴቶች የዓመቱ ምርጥ እጩዎች ዝርዝር በነገው እለት ይፋ ይሆናል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም