እነ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ በዋስ ተለቀቁ - ኢዜአ አማርኛ
እነ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ በዋስ ተለቀቁ
67
ጥቅምት 3/2012 በሰኔ 15 የባለስልጣናት ግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የነበሩት እነ ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ በዋስ እንዲለቀቁ መወሰኑን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት አስታወቀ። በመስሪያ ቤቱ የክልል አቃቤ ህግ አቶ እዮብ ጌታቸው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ግለሰቦቹ በግድያ ወንጀሉ ተጠርጥረው ማጣራት ሲካሄድ ቆይቷል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በዋስ የተለቀቁትም ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል አማረና ኮሎኔል ባምላክ አባይ መሆናቸውንም ገልፀዋል። መርማሪ ቡድኑም በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰረትና አስተያያት እንዲሰጥ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ መመራቱንና በተሰበሰበው ማስረጃ መሰረትም ለዋስትና የሚከለክል አለመሆኑን በማረጋገጥ በዋስ እንዲፈቱ ተወስኗል። እስከ አሁን በተደረገው ማጣራትና በተሰበሰበ ጥልቅ የሰው፣ የቴክኒክና የፎረንሲክ ማስረጃ በግድያው ዋና ወንጀል አድራጊነት የተሳተፉ አለመሆናቸውንና ክስ ለመመስረት የሚያስችል ማረጋገጫ ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል። “ይሁን እንጂ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ ሃላፊነት የነበራቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሃላፊነትን ባለመወጣት ይጠየቃሉ ወይስ ሊጠየቁ አይችሉም የሚለውን በቀጣይ የማጣራት ስራ ይከናወናል” ብለዋል። በመሆኑም ይህንን ለማጣራት ተጠርጣሪዎችን በማረሚያ ቤት ሊያቆያቸው የማይችል በመሆኑና በውጭ ሆነው ጉዳዩን መከታተል ስለሚችሉ በ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲቀለቀቁ መደረጉን አብራርተዋል። በነብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ክስ እንዲመሰረት ለጥቅምት 12/ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዞ እንደነበር ይታወሳል።በዚሁ መዝገብ 218 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን አብዛኛቹ ተጣርቶ መለቀቃቸውም ይታወሳል።