የሰሊጥ ምርታችንን በማህበራት በኩል ማቅረባችን ተጠቃሚ አድርጎናል - የቃፍታ ሁመራ ወረዳ አርሶ አደሮች

386
ሁመራ ሰኔ 10/2010 የሰሊጥ ምርታቸውን በማህበራት አማካኝነት ለገበያ ማቅረብ በመጀመራቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞን  ሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ የቃፍታ ሁመራ ወረዳ ነዋሪ  አቶ ጉዕሽ ብርሃነ እንዳሉት ከአሁን በፊት የሰሊጥ ምርታቸውን ወደ ገበያ የሚያቀርቡት በተናጠል በመሆኑ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡ በደላላ አማካኝነት ያካሂዱት በነበረው ግብይት ከአንድ ኩንታል የሰሊጥ ምርት  እስከ 500ብር ያጡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት አመት ግን ምርቱን ለህብረት ስራ ማህበራት ማቅረብ በመጀመራቸው  የተሻለ ዋጋ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት በበጀት አመቱ  43 ኩንታል የሰሊጥ ምርት በአከባቢያቸው ለሚገኝ ህብረት ስራ ማህበራት በማስረከብ ለአንድ ኩንታል ሰሊጥ በ4 ሺህ 355 ብር ሂሳብ እንደተሸጠላቸው ገልጸዋል፡፡ “የሰሊጥ ምርቴን በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቅረብ በመጀመሬ ደላሎች ይጠቀሙበት የነበረውን ገንዘብ ማስቀረት ችያለሁ'' ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሀፍቱ ለገሰ ናቸው፡፡ ማህበራቱ አሁን በጀመሩት ስራ ተጠቃሚ ሆነናል ያሉት አርሶ አደሩ ማህበራቱ ምርቱን በቀጥታ ወደ ውጭ መላክ ቢጀምሩ ደግሞ የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደር አስማረ ሽዋየ በበኩላቸው “የሰሊጥ ምርታቸው በቀጥታ ለህብረት ስራ ማህበራት ማስረከብ በመጀመራቸው ከእንግልትና የገበያ ውጣ ውረድ ተላቀናል'' ብለዋል፡፡ አርሶ አደሩ በምርት ዘመኑ ካመረቱት 25 ኩንታል ሰሊጥ በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ከ108 ሺህ ብር በላይ ገቢ  ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዞኑ በሚገኙ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኔኖች አማካኝነት 92 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ወደ ምርት ገበያ መቅረቡን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ  አስተባባሪ ወይዘሮ አመለ ወርቅ ወልዴ ናቸው፡፡ ይህም አርሶ አደሩ  የተሻለ  የገበያ ዋጋ ማግኘት እንዳስቻለው ገልጸዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም