በአገሪቱ ህገ-መንግስት የፀደቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሊከበር ይገባል - አስተያየት ሰጪዎች

117

ጥቅምት 3 / 2012  በኢትዮጵያ የበላይ በሆነው ህገ - መንግስት የፀደቀው የአገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሊከበር እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።

12ኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ተከብሯል።

ቀኑ በተለይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲከበር ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን፣ የምክር ቤቱ አባላትንና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫና ከታች ቀይ ቀለም ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መካከል የሚገኘው ብሔራዊ አርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እንደዚሁም ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 3 ላይ ተመልክቷል።

ሆኖም አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደሚሉት ይህ በህገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጠው የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር እያገኘ አይደለም።

የምክር ቤት አባል የሆኑት አምባሳደር ታዬ ቸርነት በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የምትወከልበት ሰንደቅ ዓላማ ተገቢው ክብር ሊቸረው ይገባል።

ሰንደቅ ዓላማው የጥንት ታሪክ ማሳያና ሉዓላዊነት መገለጫ እንዲሁም የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ተምሳሌትና የሰላም ወዳድ ህዝቦች ማሳያ በመሆኑ ተገቢው ክብር ሊኖረው ይገባል።

በሰንደቅ ዓላማው ላይ ጥያቄ ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄውን ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የማቅረብ መብት እንዳለውም ነው አምባሳደር ታዬ የገለፁት።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኢተፋ ኢባ በበኩላቸው እንደሚሉት ትውልዱ የፖለቲካንና ሰንደቅ ዓላማን ልዩነት ጠንቅቆ ይገነዘብ ዘንድ በስፋት መሰራት አለበት።

‘’ፖለቲካ ነገ ያልፋል፤ ሰንደቅ ዓላማ ግን ትውልድ ሲዘክረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲወከል ይኖራል’’ ሲሉ የሚናገሩት አቶ ኢተፋ ይህንን እውነታ ትውልዱ እንዲረዳ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በምክር ቤቱ በተሰናዳው የሰንደቅ ዓላማ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፕሬዝዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ እንደሚሉት ባንዲራ የአንድ ሃገርና ህዝብ ወኪል በመሆኑ ሊከበር ይገባል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚታየው ልዩነት ህዝቦች ሳይሆኑ  ጥቂት ፖለቲከኞች ያመጡት ትርክት ነው ብለዋል።

በተለያየ ጊዜ ከሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ጥያቄ መንግስት ህዝብ ውሳኔ አደርጎም ቢሆን መልስ የሚሰጥበትን መንገድ መዘየድ አለበት ሲሉም መክረዋል።

እንዲያም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለውን ሰንደቅ ዓላማ በህጉ መሰረት አክብሮ ጥያቄው እንዲመለስ በትዕግስት መጠበቅ ይገባል ባይ ናቸው  አቶ አየለ።

ሰንደቅ ዓላማ ለአገር ያለውን ጠቀሜታና ምንነቱን ትውልዱ እንዲያውቀው ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሊሰራ ይገባል ሲሉም አቶ አየለ አሳስበዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን  የተከበረው "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሀነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ቃል ነው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር ሰንደቅ ዓለማ የግንኙነት መለያ እንጂ የፖለቲካ መሳሪያ እንዳይሆን መከላከል ይገባል ብለዋል።

ለአዲሱ ትውልድም የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም ማስተማር እንደሚገባ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ የሰንደቅ ዓላማን አያያዝ የሚደነግጉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የሰንደቅ ዓላማን ክብር መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም