በሚቀጥሉት 10 ቀናት ደረቃማ የአየር ሁኔታ ይኖራል

476
አዲስ አበባ  ጥቅምት 3 /2012 በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። በሚቀጥሉት ቀናት አብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች የበጋው ደረቃማ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በአንዳንድ የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አጋማሽ ክፍሎች በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም የኤጀንሲው ትንበያ አመልክቷል። በተጨማሪም በጥቂት የደቡባዊው የአገሪቱ አጋማሽ ቦታዎች ከባድ ዝናብ እንደሚኖርም ጠቁሟል። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ዞኖች ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። በቀሪዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው። በአገሪቱ የሚኖረው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑ አካባቢዎች ለማሳ ዝግጅትና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው የኤጀንሲው ትንበያ አመልክቷል። እርጥበታማ የአየር ሁኔታ በሚጠበቅባቸውና የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ በሚገኙባቸው አካባቢዎች እርጥበቱ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቁሟል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም