የቱሪዝም ዘርፉን ኢኮኖሚ  የማመንጨት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው 

68

ኢዜአ፤ መስከረም 3/2012 የሀገሪቱ ከቱሪም ዘርፍ ኢኮኖሚን የማመንጨት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን  የባህልና ቱሪዝም ሚስቴር ገልጿል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ታሪኩ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት የቱሪዝም   ዘርፉን  ለማነቃቃት  በርካታ ስራዎች  እየተከናወኑ  ነው፡፡

 በማሻሻያው ስራዎቹ በባለሙያ እንዲሰሩ የሠው ሃብት አደረጃጀት መዋቅራዊ ለውጥ መደረጉን ና ዘርፉን በሁለንተናዊ  እንቅስቃሴ  ለማጎልበት  ባለፈው አመት ከተያዘለት አመታዊ  በጀት 87 ሚሊዮን ብር በዚህ አመት ወደ 137 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን  አብራርተዋል፡፡

ከቱሪዝም መመዘኛዎች መካከል ሰላምና  ጸጥታ፣ አሰሪ ና ስትራቴጂ ፖሊሲዎች፣ የተፈጥሮ ና  የባህል ሃብት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው፤ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ የዘርፉን የኢኮኖሚ  ጉድለት  ለሟሟላት  ተስፋ ከተጣለባቸው  ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን መናገራቸው  በመንግስት ትኩረት እንደተሰጠው ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀደሙት ጊዜያት ቱሪዝም እንደ ማህበራዊ ዘርፍ እንጂ እንደ ኢኮኖሚ ይታይ ስላልነበረ፤   ከተመሰረተበት ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተዳብሎ ሲሰራ በመቆየቱ ለዘርፉ ማነቆ ሆኖ እንደነበር ነው አቶ ታሪኩ ያብራሩት፡፡

በዚህ በጀት ዓመትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን  ቱሪስት በመሳብ  5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑንም ተናግረዋል።

የባለአገሩ  አስጎብኚ  ድርጅት  ስራ አስኪያጅ  አቶ ተሾመ አየለ የቱሪዝም እንቅስቃሰው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በመንግስት በኩል  ዘረፉን  ለመደገፍ የተያዘው እቅድ የተሻለ  የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር ያግዛል ነው ያሉት።

በቤተ-መንግስት ቅጥር ግቢ  የአንድነት ፓርክ ለጉብኝት ክፍት መሆኑ ለቱሪዝም  መነቃቃት  ላቅ ያለ ድረሻ  ይኖረዋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ፓርኩ ለጉብኝት  ክፍት ሆኖ ኢኮኖሚ እያመነጨ  ህብረተሰቡም የሀገሪቱን  ታሪካዊና  ባህላዊ  እሴቶችን  እንዲረዳ  በማድረግ  አንድነትን  ያጠናክራል  ብለዋል።

 “ኢትዮጵያውያን  እንኳን  ተከፍሎን ሳይከፈለን  በነጻ  እንግዳ  የምናስተናግድ  ህዝቦች  በመሆናችን  ተፈጥሯችን  ለቱሪዝም  አመችነት  አለው” የሚሉት  ስራ አስኪያጁ፤  ቱሪዝም  የማንነት  መገለጫ  በመሆኑ  የውጭ ሀገር ዜጎች  ስለ ኢትዮጵያ  ትክክለኛ ግንዛቤ  የሚኖራቸው  መጎብኘት ስችሉ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ  የማይዳሰሱ  ቅርሶች  ለሀገር  ውስጥ ቱሪዝም  መጎልበት  አስተዋጽኦ  እያበረከቱ መሆኑን የገለጹት አቶ ተሾመ፤ አንዱ ስለሌላው እንዲያውቅ ስለሚያግዝ በህዝቦች መካከል ያለውን  መስተጋብር  ያጠናክራል ነው ያሉት።

ባህል ይቅር ባይነት፣ አስታራቂ ፣  ሰላምና ፖለቲካ ጭምረ በመሆኑ፤ ለሰላም መስፈን ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የሀገር  ውስጥ ቱሪዝም  መነቃቃት ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ  ያስችላል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።

ሰላም  ከቱሪዝም  ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው ያሉት አቶ ተሾመ  ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም ሃብት  አንጻር የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት በተጨማሪ ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደጎም ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማራው ወጣት ቢኒያም ይልቃል በበኩሉ፤  በርካታ ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛትና የነጻነት ታሪክ እንደሚማረኩ ጠቅሶ፤ የአንድነት ፓርክ ለጉብኝት ክፍት መደረጉ የኢትዮጵያን ታሪክ ማወቅ ለሚፈልጉ የውጭ ቱሪስቶች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ይጠቁማል።

ቱሪዝም በባህሪው አለም አቀፍ በመሆኑ የመቻቻል፣ የእውቀትና የልምድ ለውውጥን በማቀላጠፍ ኢትዮጵያ አለም ከደረሰበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የእድገት ደረጃ ለመድረስ የምታደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያለው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም