የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ መስራት ይጠበቅባቸዋል- ሚኒስቴሩ

55
ዲላ  ጥቅምት 3 / 2012 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ዘመኑ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርበው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች የሚመራ ቡድን የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አቀባበልን ተመልክቷል። የሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር እሸቱ ከበደ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋማቱ ከየአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር ሰላማዊ  የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር  መትጋት አለባቸው። ተቋማቱ የትምህርት ዘመኑን ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር እንዲያጠናቅቁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ ተማሪዎችን ለመቀበልና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎችን  በመከታተል ድክመቶችን በማረም ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች አገልግሎትና በመሠረተ ልማት ዙሪያ ያከናወናቸው ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል። በሚኒስቴሩ የፕሮግራሞች ሥርዓተ ትምህርትና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ መኮንን በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲዎች ተቀዳሚ ተግባራቸው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማረጋገጥ ነው ይላሉ። ለቅሬታ ምንጭ የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን መስራት እንዳለበትም ተናግረዋል። ተማሪዎችም የመጡበትን ዓላማ በመረዳት ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊ እንዲሆን የጀመራቸውን ሥራዎች ከማጠናከር በተጓዳኝ በቡና ምርምር፣ በእጽዋት ጥናትና በኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ያከናወናቸው ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ ከመስራትና ከአሳታፊነት አንጻር የሚታዩ ውስንነቶችን በማስተካከል መስራት  እንዳለበትም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍቃዱ ወልደማሪያም በበኩላቸው ቡድኑ ያመላከታቸውን ክፍተቶችን ፈጥኖ በማረም የትምህርት ዘመኑን በስኬት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊ እንዲሆን ዝግጅት መደረጉንና በተማሪዎች አገልግሎት ጉድለቶችን ለማሟላት ጎን ለጎን ከመምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም