የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች አጀንዳ 2063 እንዲሳካ የሂሳብ አያያዝና አስተዳደር ስርዓታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ተባለ

65
አዲስ አበባ  ጥቅምት 3  /2012የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች አጀንዳ 2063 እንዲሳካ የሂሳብ አያያዝና አስተዳደር ስርዓታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ተባለ:: አጀንዳ 2063 አፍሪካን ወደተሻለ ደረጃ በማሸጋገር የመጪው ዘመን ተጽዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ ያለመ አካታችና ዘላቂ ልማትን መሰረት ያደረገ አህጉራዊ ስትራቴጂክ እቅድ ነው። በአህጉሪቱ የሂሳብ አያያዝ መጠናከርና ማጎልበት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፎረም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው። ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የኦዲተርና አካውንታንት ጀነራሎች፣ የሂሳብ አያያዝ ማህበራት፣ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ አስተዳደር ፎረም እንዲሁም የዓለም አቀፉ ሂሳብ አያያዝ ቦርድ ተወካዮች እየሳተፉ ነው። በሂሳብ አያያዝ ላይ የተሞክሮ ልውውጥ፣ የባለሙያዎች እይታዎችን ዳሰሳና የአፍሪካ አገሮች በመስኩ የተሻለ ስርዓት እንዲዘርጉ መንገዶችን ማመላከት የፎረሙ ዓላማ ነው። አገሮች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ሁኔታን ማመቻት ከፎረሙ የሚጠበቅ ሌላው ውጤት መሆኑ ተጠቅሷል። የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፎረሙ አገሮች ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡ ከማስቻል ባለፈ ዓለም አቀፉን የሂሳብ አያያዝ ደረጃ ለመተግበር የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል። የተቀናጀች፣ የበለጸገችና ሠላማዊ አፍሪካን መፍጠር በአጀንዳ 2063 መካተቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው ራዕዩ እንዲሳካ በፋይናንስ አስተዳደርና ሂሳሳብ አያያዝ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ወሳኝ እንደሆነ አስምረውበታል። ለዚህ ደግሞ አባል አገሮች ጠንከረው በመስራት ጠንካራ የፋይናንስ አስተዳደር በመዘርጋት ሙስናን መግታትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ማቃለል እንደሚችሉ አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያም የፋይናንስ ስርዓቱን ማጠናከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በማመን እየተሰራበት እንደሆነ ያስረዱት አቶ አድማሱ፤ ''በተለይም በመንግሥት ይዞታ ስር ባሉ የልማት ድርጅቶች ዘንድ ግልጽነት የተሞላበት አሰራር ለመተግበር ትኩረት ተሰጥቷል'' ብለዋል። እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በዋናነት ገንዘብ ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ የሂሳብ አያያዝ ስርዓት እየተከተለች ሲሆን ወደ ፊት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ የሂሳብ አያያዝ ስርዓት ለመዘርጋትና ገንዘብ ነክ ወዳልሆነ ሂሳብ አያያዝ ስርዓት ለመግባት በሂደት ላይ ትገኛለች። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ኪዌሲ ኩዋርቲ በበኩላቸው በአፍሪካ አብዛኛው የሠላም እጦት መነሻ ድህነት መሆኑን ገልጸው፤ አገሮቹ በአግባቡ የሂሳብ አያያዝና አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ ልማት ማምጣት እንደሚችሉ ገልጸዋል። ''ይህ ደግሞ አጀንዳ 2063 እንዲሳካ የራሱን ሚና ይጨወታል'' በማለት አክለዋል። በአፍሪካ በዘርፉ ግልጽ የሆነ አሰራር እንዲዘረጋ በህብረቱ በኩል የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመው አባል አገሮች አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል። ምክትል ሊቀ መንበሩ እንደሚመክሩት አገሮች ጠንካራና የተሻለ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት ወጣቶችን በሂሳብና አካውንቲግ ዘርፎች በብዛት ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል፤ በግልና በመንግሥት የቢዝነስ መስኮችም ግልጽነትን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በፎረሙ ላይ ከ200 በላይ ባለድርሻ አካላት እየተሳፉ ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ የአካውንቲንግ ጀነራል ማህበር ይቋቋሟል ተብሎም ይጠበቃል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም