በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው ---ትምህርት ቢሮ

91
ባህር ዳር ጥቅምት 3 / 2012 በአማራ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። የአማራ ልማት ማህበር ( አልማ)  ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የሙከራ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ይልቃል ከፍአለ  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ በለሳ ወረዳ ጎሃላ ከተማ የተገነቡ ከፕሮጀክቶች ሲመረቁ እንዳሉት በክልሉ 84 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የአቋሯጭ ተማሪዎችን ቁጥርም ለመቀነስ በቅንጅት በመሥራት ላይ  እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለዚህም አልማ የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ለትምህርት ተቋማት መሻሻል እገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ማህበረሰቡም የትምህርት ተቋማቱን በባለቤትነት ስሜት እንዲያግዝ  ኃላፊው ጠይቀዋል። አልማ በክልሉ በዕውቀት የዳበረ የሰው ኃይል ለመፍጠር ትኩረት መስጠቱን ያስረዱት ደግሞ የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው። አልማ ከ 2012 አሰከ 2014 የክልሉን ትምህርት ቤቶች  ደረጃ ከ16  ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ ስትራቴጂያዊ  ዕቅድ ነድፎ ትግበራ መጀመሩን አስታውቀዋል። በጎሃላ ከተማ በ23 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብተው የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የዕቅዱ ተጨባጭ ማሳያ መሆናቸውን አቶ መላኩ ገልጸዋል። በቀጣይ ዓመታትም ከአባላት በሚሳባሰብ ገንዘብ ትምህርት ቤቶቹን የማሻሻል ሥራው ይጠናከራል  ብለዋል። ኅብረተሰቡ የክልሉን የትምህርት ጥራት ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ከማህበሩ ጎን እንዲቆም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል። የቀድሞው ትምህርትቤት ለትምህርት ሥራ ምቹ ካለመሆኑ በላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ስጋት ላይ ጥሎት እንደነበር የተናገረው የ12ኛ ክፍል ተማሪው ገብረ ማርያም ሙላት ነው። በምረቃው ሥነ ሥርዓት  የክልል፣ የዞን የወረዳ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም