አልማ የጀመረውን የልማት ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ... አቶ ተመስገን ጥሩነህ

46
ጥቅምት 3 ቀን 2012 የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር (አልማ) የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የጀመረውን የልማት ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ገለፁ። "ህዝባዊ ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የአልማ 13ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጉባኤው ሲጀመር እንዳሉት አልማ የክልሉን ልማት በራስ አቅም ለመፍታት ከ4 ሚሊዮን የሚበልጡ አባላትን በማፍራት እየሰራ ነው። ማህበሩ ያከናወናቸው የልማት ሥራዎችም ባለፉት ዓመታት በክልሉ የትምህርት፣ የጤናና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት እንዲያድግ አድርጓል። ህዝቡ የሚፈልገውን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የሚያስችል ስትራቴጂክ ዕቅድ ማህበሩ ነድፎ ወደ ትግበራ መግባቱን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፣ ይህ እንዲሳካም የሁሉም አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተለይም የክልሉን የትምህርት ሽፋንና የጥራት ችግሮች ለማቃላል መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ አልማ እያደረገ ያለው ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውጤት የሚያስገኝ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ እየተከናወነ ላለው ሁለንተናዊ ልማትም ከአልማ በተጨማሪ ባለሃብቶች፣ የልማት አጋሮችና አባላት  በተጠናከረ አግባብ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል። "አልማ የተደራጀ ህዝባዊ አቅምን ለልማት በማዋል የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል" ያሉት ደግሞ የማህበሩ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ደርበው ናቸው። ማህበሩ ለአንድ ቀን እያካሄደ ባለው ጠቅላላ ጉባኤም የማህበሩን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አጋማሽ አፈጻጸም እና ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም የሚተገበረው አዲሱ ስትራቴጂካዊ የለውጥ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል። በተጨማሪም አዲስ የጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበር ምርጫና በተጓደሉ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ምትክ  ምርጫ እንደሚካሄድ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም