በትግራይ የባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ለማጠናከር እየተሰራ ነው

578
መቐለ ጥቅምት 3/2012..... በትግራይ ክልል በሃገር ሽማግሌዎች የሚደረግ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በማጠናከር በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ ። በክልሉ በዓመት በአማካይ 50 ሺህ የክስ መዝገቦችን በሽምግልና እንዲያልቁ ለማድረግ ታቅዷል ። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕረዚዳንት አቶ ተስፋይ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት በአገር ሽማግሌዎች በእርቅ ሊፈታ የሚችል የማህበረስብና የግለሰቦች ግጭት ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እየመጡ በአሰራር ላይ የስራ ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን  ገልፀዋል ። በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 232 ሺህ የክስ መዛግብት በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲሰጣቸው መደረጉን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ይህም ከቀዳሚው አመት ጋር ሲነፃፀር  በ47 ሺህ የክስ መዛግብት የሚበልጥ መሆኑን  አስረድተዋል። የክስ መዛግብት ለመጨመር ምክንያት ናቸው ተብለው የተቀመጡ ደግሞ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት  ለመከላከል የተደረገው ጥረት አናሳ መሆንና ለባህላዊ የግጭት አፈታት ተገቢውን ትኩረት አለመሰጠቱ ነው ብለዋል ። በክልሉ በራያ አዘቦ፤ ራያ አላማጣ፤ኦፍላ፤ህንጣሎ ዋጅራት፤አፅቢ ወንበርታና ኢሮብ ወረዳዎች ለብዙ ዓመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልት እንዳላቸው ተናግረዋል። አሁን በውስን ወረዳዎች እየተሰራበት ያለው ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በሁሉም ወረዳዎች ለማስፋፋት ስራ መጀመሩን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልት በትምህርትና በስልጠና ለመደገፍ  በፍትህና ጸጥታ ዘርፍ የሚሰሩ አስር አስተባባሪ አካላት የጋራ እቅድ ማውጣታቸውን አስረድተዋል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ወጪ ቆጣቢና አገር በቀል እውቀትን ተግባራዊ የሚያደርግ በመሆኑ በህብረተሰብ ያለው ተቀባይነት ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ይህን ተግባራዊ በማድረግ በየአመቱ ከ50 ሺህ ያላነሱ የክስ መዛግብት ለመቀነስ እቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል። ህዝቡ በረባና በማይረባ ጉዳዮችን የልማት ስራውን ትቶ እየተካሰሰ ከሚውል በባህላዊ እርቅ እንዲጠናቀቅ የተጀመረው ስራ የሚደገፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር መኮነን ካህሳይ ናቸው። ለድህነት ከሚያጋልጡ ጉዳዮች መካከል በረባና ባልረባ ጉዳዮች ህብረተሰቡ ከቦታ ወደ ቦታ መንከራተት በመሆኑ ጊዜውን በአግባቡ ለልማት ስራ እንዲያውል ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃለፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኙ የህግ ባለሙያዎች ቀለል ያሉ ጉዳዮችን በሽምግልና እንዲጠናቀቁ የማድረግ አቅጣጫ እንዲከተሉ ይደረጋል ብለዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም