ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ'ቻንግዙ ዌስት ታይሁ ሌክ' ግማሽ ማራቶን ደማቅ ድል አስመዘገቡ

84
ጥቅምት 3/2012 ትናንት በቻይና በተካሄደው ቻንግዙ ዌስት ታይሁ ሌክ የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል በበላይነት አጠናቀዋል። በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ድረስ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። በወንዶች አትሌት ታዬ ግርማ 1 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን የባለፈውን ዓመት ውድድር ሲያሸንፍ የያዘውን ክብረ ወሰን በ19 ሴኮንድ አሻሽሏል። አትሌት አብዲ ፉፋ 1 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣ ሲሆን በርቀቱ ሁለተኛ የግል ምርጥ ሰአቱን ማስመዝገብ ችሏል። በውድድሩ ላይ ከተሳተፉት አትሌቶች መካከል በ1 ሰዓት ከ00 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ የተሻለ የግል ምርጥ ሰአት የነበረው አትሌት አሰፋ ተፈራ  1 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በሴቶች አትሌት ፋንቱ ጅማ 1 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን በባለፈው ዓመት ውድድር በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ዘነቡ ፍቃዱ የተያዘውን ክብረ ወሰንም በ1 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ አሻሽላለች። አትሌት እታገኝ ወልዱ 1 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ሁለተኛ፤ አትሌት ዝናሽ መኮንን 1 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በሴቶች ሁለተኛና ሶስተኛ የወጡት አትሌቶች በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸውን ማስመዝገብ ችለዋል። ኢትዮጵያን አትሌቶች በቻንግዙ ዌስት ታይሁ ሌክ የግማሽ ማራቶን ውድድር ታሪክ በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ የዘንድሮው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል። ለስድስተኛ ጊዜ የተካሄደው የቻንግዙ ዌስት ታይሁ ሌክ የግማሽ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም