በበጋ ወቅት በቂ የጎርፍ መከላከል ስራ ባለመሰራቱ ስጋት ፈጥሮብናል - የውቅሮ ማራይ ከተማ ነዋሪዎች

58
አክሱም ሰኔ 10/2010 በበጋ ወቅት በቂ የጎርፍ መከላከል ስራ ባለመሰራቱ ስጋት እንደፈጠረባቸው በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የውቅሮ ማራይ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት በከተማዋ ያለው የጎርፍ ስጋት ለመከላከልና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የከተማው ማዘጋጃ ቤት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ አይደለም፡፡ የከተማዋ  ነዋሪ አቶ ገብረማርያም ሓጎስ በሰጡት አስተያየት  በቂ የጎርፍ መውረጃ ቦይ ባለመሰራቱ በከተማዋ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች በጎርፍ እየተበላሹ ነው፡፡ በተለይም  ከተራራ የሚወርደው ጎርፍ  ቆሻሻዎች እያመጣ የከተማዋ ውበት ከማበላሸቱ ባለፈ ለጤና ጠንቅ  እየሆነባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል። ባለፉት ሶስት ቀናት በጣለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ በቤታቸው ገብቶ ንብረት እንዳበላሸባቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ ገብረህይወት ሓጎስ  የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡ ጎርፉን ለመከላከል ህብረተሰቡ የበኩሉን ስራ እየሰራ ቢሆንም ከማዘጋጃ ቤቱ ድጋፍ ባለማግኘቱ ውጤት እያመጣ እንዳልሆነና ከስጋት ለመላቀቅ እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ በንግድ ስራ የተሰማራች ወጣት ሙሉብርሃን ገብረሚካኤል በበኩሏ ሃይለኛ ዝናብ በዘነበ ቁጥር በስራ ቦታዋ ጎርፍ እየገባ  ንብረት እየተበላሸባት መሆኑን ገልጻለች፡፡ አቶ  ጸጋይ መኮነን በበኩላቸው  ባለፉት ሁለት አመታት በአካባቢያቸው በተከናወኑ ተግባራት የጎርፍ ስጋቱ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም ዘላቂ መፍትሄ እንደላገኘ ተናግረዋል፡፡ የውቅሮ ማራይ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ዲያቆን አብርሃ ተወልደ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ነዋሪዎቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከተማ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስራ አስኪያጁ እንዳሉት በየአመቱ ህብረተሰቡ በሚያደርገው የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የጎርፍ ስጋት እየቀነሰ መጥቷል። ችግሩን በዘላቂ ለመፍታት ደረጃ በደረጃ እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ በዚህ አመት በ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ ከተራራው የሚወርደውን ጎርፍ የመውረጃ ቦይ  መሰራቱን በአብነት ገልጸዋል። የታሕታይ ማይጨው ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ብርሃነ በበኩላቸው በከተማዋ የጎርፍ ስጋትን ለመከላከል በቀጣይነት በጀት ተይዞለት  ዘላቂ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም