በአገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት ሕግን አክብረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል-ባለስልጣኑ

62
አዳማ  ጥቅምት 02 ቀን 2012 በአገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት ሕግን አክብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በማክበርና በማስከበር ረገድ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት የምክክር መድረክ በአዳማ አካሂዷል። በባለስልጣኑ የሚዲያ ልማትና ጥናት ቡድን መሪ አቶ ሁሴን ሻንቆ እንደገለጹት በአገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ባለሙያዎቹና ተቋማቱ ከማንም ተፅእኖ ነፃ ሆነው ሕግን አክብረው መሥራት አለባቸው። ባለስልጣኑም በጋዜጠኞቹና በተቋማቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ከባለድርሻ  አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህም በሕግ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በማስጠበቅ፣ ከሕግ አንፃር ያሉባቸው ክፍተቶች ለመሙላት፣የአቅም ውስንነትና የግንዛቤ እጥረት ለማስወገድ ጥረት እያደረገ  ነው ብለዋል። የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማቱ ሙያውንና ሕግን መሠረት አድርገው የሚሰሩባቸው አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን ጭምር የሚለውጡ የሕግ ማዕቀፎች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ቡድን መሪው አስረድተዋል። ባለስልጣኑ በሚዲያ ተቋማት ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለማስወገድ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ሁሴን፣ የድጋፍና ክትትል ፣የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል። መድረኩ ሙያውን ከሕግ እይታ አንፃር በመቃኘት በሕግ የተደነገጉ አሰራሮች፣ዓዋጆችና ደንቦች ላይ ክህሎት ለማስጨበጥ መዘጋጀቱን አመልክተዋል። የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች በሕግ ተጠያቂነት ላይ ያላቸው ክህሎትና ግንዛቤ አናሳነት ችግር እንዳጋጠመ የገለጹት ደግሞ የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለ ገብርዔል ናቸው። የኤሌክትሮኒክስ፣የኅትመትና ማህበራዊ ሚዲያ ሕጎች አስቻይና ተጠያቂነት እንደሚያስከትሉ ባለስልጣኑ ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ተቋማቱና የዘርፉ ባለሙያዎች በተለይም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር ሕዝቡን የማሳወቅ ድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል። ጋዜጠኞች ገለልተኛ ሆነው ለሙያቸው ተገዥ ሆነው ሕዝቡን ከማገልገል ይልቅ፤በግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ተፅእኖ ሥር መውደቃቸውን አቶ ደበበ ተናግረዋል። ባለሙያዎች የአቅም፣የዕውቀትና የግንዛቤ ክፍተት፣የሥነ ምግባርና የሕግ ጥሰቶች እንደሚስተዋሉባቸው አመልክተዋል። ''ሐሳብን በነፃነት መግለፅ ሲባል የሕግ ተጠያቂነት አይኖርም ማለት አይደለም'' ብለዋል። መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በራሳቸው  የሚተማመኑና ለሙያቸው ተገዢ  ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማትና ለመፍጠር  በትብብር እንዲሰሩ አስገንዝበዋል። በአዳማ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ ከግልና ከመንግሥት የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም