ኢንስቲትዩቱ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማስፋፋት ጥረት እያደረግኩ ነው አለ

61
አዳማ ጥቅምት 2 ቀን 2012 በአገሪቱ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ መሆኑን የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው የ2012 በጀት ዓመት የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በዚሁ ወቅት እንደተናገሩትት ኢንስቲትዩቱ የቱሪዝም ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራ ነው። በዚህም በስልጠና፣ምርምርና የምክር አገልግሎት በመስጠት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ለማሟላት የገበያውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ሰልጣኞችን ለማፍራት እየሰራ ነው ብለዋል። በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት፣ አሰራሮችን ለማዘመንና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ጥናቶችና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ላይ ማትኮሩን  ዋና  ዳይሬክተሯ አስረድተዋል። በዚህ ረገድ ካለፈው ዓመት ወዲህ በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች፣በአዲስ አበባና በክልሎች ያሉትን ተግዳሮቶችን ለመለየት ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም 27 የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከ13 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል። ይህም የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪውንና የስልጠና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል እንደሚያስችል ወይዘሮ አስቴር ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ ደረጃውን የጠበቀ ባለአምስት ኮከብ ሆቴልና የተማሪዎች ማደሪያ ስለሌለውና  የሚከፍለው የኪስ ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ ሰልጣኞች ወደ ኢንዱስትሪው እንዳይመጡ ተግዳሮት እንደሆነበት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን አካዳሚ ተወካይ አቶ ዋለ ይሁኔ በሰጡት አስተያየት አካዳሚው ከኢንስቲትዩቱ ጋር በፈጠረው ግንኙነት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም በተለይ የበረራ አስተናጋጆች የምግብና መጠጥ መስተንግዶውን በጥራት ለማከናወን እንደሚያስችለው አስታውቀዋል። ለሁለት ቀን በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራልና ከክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያገለገለ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ15 የስልጠና መስኮች እስከ መጀመሪያ ዲግሪ  ደረጃ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም