የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብ አገራዊውን ለውጥ ለማስቀጠል ከለውጥ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠየቁ

61
አሶሳ ጥቅምት 02 ቀን  2012 በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ሕዝቡ ከለውጥ ኃይሉ ጎን እንዲቆም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ያገኙትን የኖቤል የሠላም ሽልማት አስመልክቶ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በአገር ደረጃ የተያዘውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የክልሉ ሕዝቡ ከአመራሩ ጎን ሊቆም ይገባዋል። በአገሪቱ በሚካሄደው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ  ዋልታ ረገጥ ሃሳቦች የሚያራምዱ መኖራቸውን አመልክተው፣እነኚህን የአስተሳሰብ ሳንካዎችን በመቀየር አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ከፍታ ለማሸጋገር ከለውጥ ኃይሉ ጎን በመሆን መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ወደ ሥልጣን በመጡበት አጭር ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ የተመዘገበው ለውጥ የሚደነቅ ነው ያሉት አቶ አሻድሊ፣በኖቤል ኮሚቴው ተመርጠው ያገኙት ሽልማት አገሪቱ የምትከተለው የለውጥ ጎዳና ትክክለኛነትን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አቶም ሙስጠፋ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ያገኙት ሽልማት አመራር የቆዩበት ጊዜ አጭር ቢሆንም፤ ከአገር አልፈው ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን ፍቅርንና አንድነትን መሠረት ያደረገ ውጤታማ ሥራዎች ማከናወናቸውን አመልክተዋል። በድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሲቱ ያሲን እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ያሳዩንን ፍቅር የተሞላበት አመራር አርአያነት በመከተል የአሶሳን ሠላም ለማጠናከር እንሠራለን ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ወርቄ ፈይሳ በበኩላቸው ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገሪቱ ብሄር/ብሄረሰቦች የተሰጠ በመሆኑ በቀጣይም አንድነትና ሠላምን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም