የካቢኔ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የወርቅ ሀብል አበረከቱ

89
ጥቅምት 2/2012 የሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ የወርቅ ሀብል አበርከቱላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ለ20 አመት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ2019 የኖቤል የሰላም አሸናፊ መሆናቸው ከትናንት በስቲያ መገለጹ ይታወቃል። ዛሬ ማለዳ የካቢኔ አባላቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው ደስታቸውን መግጻቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አባላቱ ለአመራሩ እንዲሁም ለተገኘው ስኬት ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽ የወርቅ ሀብል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱ ሲሆን "እውነት ፍቅር ያሸንፋል" የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺህ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ። በአጠቃላይ በዘንድሮው ውድድር 301 እጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም