የአሰላ ብቅል ፋብሪካ በአርሶ አደር ማህበራት እንዲተዳደር መደረጉ የማምረት አቅሙን አሳድጎታል

60
ጥቅምት 2/2012 የአሰላ ብቅል ፋብሪካ በአርሶ አደር ማሕበራት እንዲተዳደር መደረጉ የፋብሪካውን የማምረት አቅም እያሳደገው መሆኑን የፋብሪካው ዋና ዳይሬክተር ገለፁ። የአርሶ አደሩን የገብስ ምርታማነት ለማጠናከር 50 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል። ላለፉት 36 ዓመታት የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ ሲሰራ የነበረው የአሰላ ብቅል ፋብሪካ 360 ሺህ ኩንታል ብቅል የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም እያመረተ ያለው ግን ከአቅሙ እጅግ ያነሰ ነበር። ለዚህም አንዱ ምክንያት ለብቅል ምርት የሚያስፈልገው የገብስ አቅርቦት አነስተኛ መሆን ይጠቀሳል። ሆኖም ፋብሪካው ለኦሮሚያ የግብርና ሕብረት ስራ ማሕበራት ፌዴሬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ ማሕበር በጨረታ ከተላለፈበት ግንቦት ወር 2010 ዓም ጀምሮ የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ መሆኑን የፋብሪካው ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ መኮንን ገልፀዋል። ገብስ አምራች አርሶ አደሩ ለፋብሪካው የሚያቀርበው የገብስ መጠን በእጅጉ መጠናከሩ ለአፈጻጸሙ መሻሻል አንዱ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ፋብሪካው በፌዴሬሽኑ ስር እንዲተዳደር መደረጉ በቀደሙት ዓመታት የነበረውን ምርታማነት በአስር በመቶ ለማሳደግ አስችሎታል። ባለፈው አንድ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ይህ አፈጻጸም ቀጣይነት እንዲኖረውም እርምጃ እየተወሰደ ነውም ብለዋል። አርሶ አደሩ ለፋብሪካው የሚያቀርበው የገብስ ምርት በበቂ ሁኔታ ያቀርብ ዘንድ የግብአት እጥረት እንዳይገጥመው ለሕብረት ስራ ማሕበራቱ 50 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ለአብነት በማንሳት። ለአርሶ አደሩ የተደረገውን ድጋፍ ተከትሎ ከአንድ ዓመት በፊት ለፋብሪካው ይቀርብ የነበረው 140 ሺህ ኩንታል ያህል ገብስ በአሁኑ ወቅት ወደ 410 ሺህ ኩንታል ሊያድግ መቻሉን ገልፀዋል። ይህም ፋብሪካው በሙሉ አቅም የሚሰራበትን ሁኔታ የፈጠረለት ከመሆኑም በላይ የብቅል ገብሱን የሚያቀርቡት አርሶ አደሮች ተጠቃሚነትንም አሻሽሎታል ብለዋል። ፋብሪካው በመንግስት ስር በሚተዳደርበት ወቅት ለገብስ ግዢ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይወጣ ነበር፤  በ2007 እና በ2008 ዓም ብቻ እንኳ 13 ሚሊየን ዶላር ለገብስ ግዥ ወጪ ሆኗል ብለዋል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ታቅፈው ምርታቸውን ለፋብሪካው ከሚያቀርቡት አርሶ አደሮች መካከል ሀብታሙ ለማ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት ከፋብሪካው ጋር በቅንጅት መስራት በመጀመሩ የገበያ ችግር እንዳይኖር እያገዘ ነው። ፋብሪካው የአርሶ አደሩ የሕብረት ስራ ማሕበራት ንብረት ቢሆንም በግብአትና በሌሎች መስኮች የሚያደርገው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ፋብሪካው የአርሶ አደሩን የገብስ ምርታማነት ለማጠናከር የገንዘብ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር የቅርብ  ክትትል ማድረግም ይጠበቅበታልም ብለዋል አርሶ አደሩ። ይህም አርሶ አደሩ ምርቱን በጥቂት ገንዘብ ተታሎ ለሕገወጥ ነጋዴዎች  እንዳይሸጥ፤ ጥራት ያለው የገብስ ምርትን በአግባቡ እንዲያቀርብ ያግዘዋል ብለዋል። ሌላው የማሕበሩ አባል አቶ አቡ ጀማል እንደሚሉት ደግሞ የዘርና ሌሎች ግብአቶች አቅርቦ እጥረት አርሶ አደሩ የገብስ ምርቱን በሚፈለገው መልኩ እንዳያቀርብ ተግዳሮት ሆኖበት ቆይቷል። በዚህም የተነሳ አርሶ አደሩ በአነስተኛ ገንዘብ ጭማሪ የገብስ ምርቱን ለነጋዴዎች ያስረክብ ነበር ብለዋል። ሆኖም ፋብሪካው ወደ ፌዴሬሽኑ ከዞረ በኋላ በዚህ ረገድ በተወሰነ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነናል ነው የሚሉት። የኦሮሚያ የግብርና ሕብረት ስራ ማሕበራት ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አስከበረች በላይነህ በበኩላቸው አርሶ አደሩ ፋብሪካውን በባለቤትነት ማስተዳደር ከጀመረ አንስቶ ጥሩ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል። ፋብሪካው ወደማህበሩ ከመተላለፉ በፊት 900 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኩንታል ገብስ በአሁኑ ወቅት ዋጋው በእጥፍ ያህል አድጓል። የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የተመሰረተው በ1976 ዓም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም