በኦሮሚያ ባሌ እና ሰሜንነዋሪዎች ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገለጹ

43
ጎባ/ፍቼ ኢዜአ ጥቅምት 2/2012፡- በኦሮሚያ ባሌ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ በባሌ ሰዌና ወረዳ በተካሄደው ሰልፍ ከተሳተፉት ነዋሪዎች  መካከል  አርብቶ አደር አቶ ሰፊ ረሺድ ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። አቶ ሰፊ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ተባብረው የዶክተር አብይ የመደመር እሳቤን በአግባቡ ስራ ላይ ካዋሉ  በሁሉም መስክ ማሸነፍ እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ነው። ሌላው የወረዳው ነዋሪ ወጣት በከር አደም በበኩሉ ዶክተር አብይ የኖቤል ሽልማት በማሸነፋቸው  መደሰቱን ገልጾ በቀጣይነት እንደ ሀገር ዴሞክራሲን የማስፋትና ሰብዓዊ መብትን የማስከበሩ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም መስራት እንደሚጠበቅበት አመልክቷል። ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለማስቀጠል ከዶክተር አብይ ጎን በመሰለፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡ የኖቤል ሽልማቱ በቀጣይነት በሀገር ደረጃ የተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ በማስቀጠል የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ሰላማዊነቱ እንዲረጋገጥ ብሎም በልማት ለማስተሳሰር የተጀመሩ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ እንዲቀጥል ጭምር የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ መምህር ጣሃ ቱሪ ናቸው፡፡ “በዶከተር አብይ አህመድ መሪነት ኢትዮጵያ ብዙ ድሎችን እንዲታስመዘግብ የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ “ብለዋል፡፡ ሽልማቱን ተከትሎ ዛሬ ነዋሪው ደስታውን በመግለጽ ሰላማዊ ሰልፉን ያደረገው በባሌ ዞን ሮቤና ጎባ ከተሞች እንዲሁም በ18 ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ጋረደው ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በሰልፉ ከዶክተር አብይ ጋር መጪው ዘመን ብሩህ ነው፣ ሽልማቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊያንና የአፍሪካዊወን ጭምር ነው፣ ሽልማቱ ከከባድ ኃላፊነት ጋር ለኢትዮጵያኖች የተሰጠ ስጦታ ነው የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ የደስታ መግለጫ ሰልፍ በባህላዊ የፈረስ ትርኢት ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን በዚህም ወጣቶች ፣ ሴቶች፣ ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና አርሶ አደሮች በባህላዊ ጭፈራና መፈክር በማሳማት ተሳትፈዋል። ከሰልፈኞቹ መካከል የፍቼ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ማሞ በላቸው በሰጡት አስተያየት “ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቆሙለት የሀገር ሰላም፣ አንድነትና ይቅርታ መሰረት የሚጥል ነው “ብለዋል። የሰላሌ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወጣት ሴኔሳ ነጋሹ በበኩሉ ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር የሥራ ጊዜ ለኢትዮጵያና ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ለሰላም መስፈን ያደረጉትን አስተዋፅኦ አለም የተገነዘበበት መሆኑን ተናግሯል። ለሀገሪቱ ገፅታ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኩራት እንደሆነ ገልጿል። ሰልፈኞቹ የዶክተር አብይ አህመድ ሽልማት የሕዝብ ትግል ውጤት ነው፣ ህዝቡ ለአንድነት ፣ለፍቅርና ይቅርታ ዘብ ይቆማል፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት አይቻልም የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብተዋል። የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ብርሃኑ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቆሙለት ዴሞክራሲ፣ፍትህ ፣እኩልነትና መደመር ሁሉም እንዲሰራ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። “በተለይ የሀገሪቱን ገፅታ በአለም አደባባይ በማጉላት የሀገሪቱ ሕዝቦች ከመከፋፈልና ከመነጣጠል ለአንድነት ለሰላምና መቻቻል ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም