በቁፋሮ የተገኘው ከተማ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው

90
ሽሬ ኢዜአ ጥቅምት 02/12ዓ.ም በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አቅራቢያ ልዩ ስሙ ‘’ማይአድራሻ’’ በተባለ አከባቢ ከአራት ዓመት በፊት በቁፋሮ የተገኘው ጥንታዊ ከተማ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ጥንታዊው ከተማ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች አገልግሎት እንዲውል የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጥንታዊ ከተማው በ2007 ዓ.ም በካሊፎርኒያ የስነ ቁፋሮ (አርኪኦሎጂስት) ባለሙያዎች በቁፋሮ የተገኘ ነው። ጥንታዊ ከተማው ከክርስቶስቶስ ልደት በፊት 1 ሺህ 250 ዓመት እድሜ ያለው መሆኑን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ምክትል ሓላፊ አቶ ሓጎስ ገብረትንሳኤ ገልፀዋል። ጥንታዊ ከተማው የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በቁፋሮና በምርምር የተገኙ ጥንታዊ የመገልገያ ቁሳቁሶችን የመሰብሰብና የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል ። በጥንታዊ ከተማው ክልል ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ አባወራና እማወራ አርሶ አደሮች ተገቢውን የካሳ ክፍያ በመፈፀም ከአካባቢው ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ የማዛወር ሥራም እየተከናወነ ነው ። ከአርሶ አደሩ ጋር መግባባት ከመፈጠሩ ባለፈ ጥንታዊው ከተማው ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው የበኩላቸው ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ። አርሶ አደሮቹ በጥንታዊ ከተማው በቁፋሮ የተገኙትን መኖሪያ ቤቶችና በውሳጣቸው የያዝዋቸው የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶቸን እንዳይጠፉና እንዳይበላሹ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ እያከናወኑ ናቸው ተብሏል። ቀደም ሲል በግንዛቤ እጥረት የተነሳ በመሬት ስር ተቀብረው የነበሩ ጥንታዊ ቤቶች ወርቅና ሌሎች የከበሩ ድንጋዮች ይገኙባቸዋል በሚል ግምት በአካባቢው ነዋሪዎች ቢፈራርሱም በስነ ምድር ቁፋሮ ስራው በጥንቃቄ የተገኙት 12 መኖሪያ ቤቶች ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደርስባቸው ተገቢ ጥበቃ እየተደረገባቸው ነው። ለአከባቢው አርሶ አደሮችም በቅርሶቹ አጠባበቅ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል ብለዋል ኃላፊው። ቅርሱን በመንከባከብ ሥራ ላይ ከሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ መብራህቱ በላይ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ጥንታዊ ከተማው የማንነታችንና የታሪካችን ጉልህ አሻራ ማሳያ በመሆኑ ተንከባክበን ለመጪው ትውልድ እናስተላልፋዋለን ብለዋል። “በቁፋሮ የተገኘው ጥንታዊ ከተማ በመንከባከብና በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ከእኔ የሚጠበቅ ሁሉ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ” ያሉት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ ቄስ እምሩ ተክለሃይማኖት ናቸው። በጥንታዊ ከተማው ክልል ውስጥ የሚኖሩ ወይዘሮ ምፅላል አብርሃ በበኩላቸው ጥንታዊ ከተማው ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ እንዲሆን ከአካባቢው ለመነሳት ፈቃደኛ ነኝ ብለዋል። ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማው ለቱሪስቶች መዳረሻ እንዲውል የታሰበው ስራ ከልብ እንደሚደግፉትም ነው የተናገሩት ። ጥንታዊ ከተማው በተያዘው ዓመት የቀሩትን የቁፋሮና ሌሎች ሥራዎች በማጠናቀቅ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል። በሚስ ዊሊክ ወንድሪች የሚመራ የካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ የስነ ቁፋሮ ባለሙያዎች በቁፋሮ በተገኘው በዚሁ ጥንታዊ ከተማ ከሸክላ የተሰሩ የተለያዩ ጥንታዊ የቤት ቁሳቁሶች ፣ ብረት የሚያቀልጥ መሳሪያና ሌሎች የታሪክ አሻራዎች መገኘታቸውን ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም