በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ከመንግስት ጋር የፖለቲካ ልዩነት አይኖረንም፡ -ፖለቲከኞች

59
ጥቅምት 1/2012 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመንግስት ተሻጋሪ የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ ግንባታው ላይ የፖለቲካ ልዩነት እንደማይኖራቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። ፖለቲከኞቹ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የህዝቡን የልማት ጥያቄ እንዲመልስ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። ከእያንዳንዱ ዜጋ በተሰበሰበ ገንዘብ ግንባታው እየተከናወነ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጋራ ፕሮጀክት በመሆኑ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጋራ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ መነሻ በመሆኗ ከታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በተሻለ ሁኔታ ከውሃው የመጠቀም ህጋዊና ተፈጥሯዊ መብቷን ለዘመናት ሳትጠቀም መቆየቷ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቁጭት ነው። የአባይ ውሃ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከበፊትም ጀምሮ በጋራ እንጂ ብቻዬን ልጠቀም የሚል ግትር አቋም እንደሌላት የገለጹት አቶ የሽዋስ ግድቡ የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች ጥቅም ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች አገሮችም ልማት የሚጠቅም እንደሆነም ተናግረዋል። የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሞያና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን ይህም አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ብለዋል። የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የፖለቲካ ድርጅቶች የድርሻቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የፖለቲካ አመለካከታቸውና ልዩነታቸው እንደማይገድባቸው ገልጸዋል። የቀድሞው የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው የአባይ ውሃን በመጠቀም የአገሪቷን ልማት ማፋጠንና የዜጎችን የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ የሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማ እንደሆነ ገልጸዋል። ''የግድቡ ግንባታ ሂደት ችግር የነበረበት ቢሆንም በተለይ ፖለቲከኞች አሁን ላይ ችግሮችን ለማረም የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍና ግድቡ እንዲጠናቀቅ ርብርብ የምናደርግበት ጊዜ ነው'' ብለዋል። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እንዳሉትም ታላቁ ግድብ የአንድ ወቅት የመንግስት ወይም የፓርቲ ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ የሀገር ሃብትና የልማት ፕሮጀክት ነው። ''ግድቡን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ማድረግ ራስ ወዳድነት ነው'' ሲሉም ተናግረዋል። ፖለቲከኞች በብዙ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ግን ልዩነት ሊኖር እንደማይገባ አስረድተዋል። ከስምንት ዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 68 በመቶ የደረሰ ሲሆን ለግንባታው እስካሁን 99 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ግንባታውን ለማጠናቀቅ 40 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም