የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ሽልማት በማስመልከት የፊታችን እሁድ በመላ ኦሮሚያ የደስታ መግለጫ ሰልፎች ይካሄዳሉ

99
አዲስ አበባ  ኢዜአ መስከረም 30 / 2012 የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የሰላም የኖቤል ሽልማት በማስመልከት የፊታችን አሁድ በመላ ኦሮሚያ የደስታ መግለጫ ሰልፎች የሚደረጉ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ሕዝብ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሽልማት በማስመልከትም የደሰታ መግለጫ መልእክት አስተላልፏል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የሰላም የኖቤል ሽልማት በማስመልከት አሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ዞኖች፣ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የደሰታ መግለጫ ስልፎች ይደረጋሉ ተብሏል። የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በሰጡት መግለጫ ድሉ የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ ድል ነው ብለዋል። ይህ ትልቅ እውቅና የተገኘው ሕዝቡ አንድነቱን በማጠናከሩና በመደማመጡ የመጣ ትልቅ ድልም መሆኑን ተናግረዋል። ''ይህ የተገኘው ድል እጥፍ ክብርና ድል ነው'' ያሉት አቶ ዴሬሳ የክልሉ ህዝብ ደስታው ከተነገረ ጀምሮ በተለያዩ መልኩ ስሜቱን እየገለጸ ይገኛል ብለዋል። በተለይ ደግሞ የክልሉ ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ደስታውን ለመግለጽ በተለያየ መልኩ ጥያቄዎችን እያቀረበ ይገኛል ነው ያሉት። የክልሉ መንግስት ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሕዝቡ በተናበበና በተቀናጀ ሁኔታ ደስታውን እንዲገልፅ ይደረጋል ብለዋል። ለሰልፉ አስፋለጊው የፀጥታ ጥብቃ ተደርጎለት በቀጣይ እሁድ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚካሄድ ይሆናል ነው ያሉት አቶ ዴሬሳ። በቀጣይም የተሻለ ድል እና ውጤት ይገኝ ዘንድ ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ እንዲሄድም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም