በምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ተፎካካሪዎች የነሐስ ሜዳሊያ አገኙ

67
አዲስ አበባ ሰኔ 10/2010 በጂቡቲ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት ለይኩን መስፍንና ፌቨን ገብረመስቀል የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን ከሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጂቡቲ ሲያካሂድ የነበረው ውድድር ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል። የኢትዮጵያ የቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተጋጣሚዎቻቸው ጠንካራና ተመጣጣኝ ፉክክር ያደረጉት ለይኩን መስፍንና ፌቨን ገብረመስቀል ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። ለይኩን ሶስተኛ በመውጣት ካገኘው የነሐስ ሜዳሊያ በተጨማሪ የ600 ዶላር የገንዘብ ሽልማት ያገኘ ሲሆን ፌቨን ገብረመስቀል ሶስተኛ በመውጣቷ የ250 ዶላር ሽልማት ማግኘቷን ተናግረዋል። ለይኩን መስፍን በዘጠኝ ጨዋታዎች 6 ነጥብ 5 ነጥብ የሰበሰበ ሲሆን ፌቨን ገብረመስቀል በአምስት ጨዋታዎች 2 ነጥብ 25 ነጥብ አግኝታለች። በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ልደት አባተ አራተኛ ስታጠናቅቅ፣ በወንዶች ፊዴ ማስተር አይዳኙም ግዛቸው በደረጃ ከሚበልጡት የግብጽ የቼስ ግራንድ ማስተሮች ሄሻም አብዱራህማንና ፋውዚ አድሃም ጋር ባካሄደው ጨዋታ አቻ በመውጣት ድንቅ ውጤት ቢኖረውም የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ሳይገባ አምስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት እንዳለ መኮንንና ኤርሚያስ ተክለማርያም በቅደም ተከተል 16ኛና 18ኛ ደረጃን መያዛቸውንም አስታውቀዋል። በውድድሩ በወንዶች የግብጽ የቼስ ግራንድ ማስተሮች ሄሻም አብዱራህማንና ፋውዚ አድሃም በሴቶች የግብጾቹ የቼስ ግራንድ ማስተሮች ሞታዝ አያህና ኢላንሳሪ ኤማን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በአጠቃላይ በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ አምስት ለወጡ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን ነው አቶ ሰይፈ ጠቁመዋል። በሁለቱም ጾታዎች ያሸነፉት የግብጽ ተወዳዳሪዎች በ2018 በሚካሄደው የዓለም የአገሮች የቼስ ሻምፒዮና ይሳተፋሉ። በውድድሩ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት አበረታች የሚባልና ለስፖርቱ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን አክለዋል። ባለፈው ዓመት የምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በጅማ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም