የአእምሮ ጤና ችግርን ለመከላከል ፈርጀ ብዙ ምላሽ ያስፈልጋል-የጤና ሚኒስቴር

72
አዳማ ኢዜአ መስከረም 30 ቀን 2012 በሃገሪቱ የአእምሮ ጤና ችግርን ለመከላከል ፈርጀ ብዙ ምላሽ እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። “የዓለም የአእምሮ ጤና ቀንን” በማስመልከት ሚኒስቴሩ  ያዘጋጀው የማነቃቂያ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ የፕሮግራም ዘርፍ አማካሪ ዶክተር ስለሺ ጋሮማ በወቅቱ እንዳስታወቁት የአእምሮ ጤና ችግሮች በአንድ ሴክተር እንቅስቃሴ ሊፈታ አይችልም። "ችግሩ ፈርጀ ብዙ ምላሽ ይጠይቃል" ያሉት ዶክተር ስለሺ በተለይ ለአእምሮ ጤና መጎልበትና በበሽታው ለሚሰቃዩ ህሙማን ምላሽ ለመስጠት የሁሉም አካል ተሳትፉ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ። በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ እንዳልሆነ በጥናት መረጋገጡን አመልክተው  በተለይም ችግሩ በዝቅተኛና መካከለኛ እድገት ደረጃ ላይ በሚገኙ ሀገራት ዜጎች ላይ በስፋት እንደሚከሰት ጠቅሰዋል። ሚኒስቴሩ በሃገሪቱ  የአእምሮ ጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች የተሻለ እንክብካቤና ድጋፍ ለመስጠት ብሄራዊ የአእምሮ ጤና ስትራቴጂ ቀርፆ እየሰራ  ነው። በየደረጃው ባሉ የጤና ተቋማት ውስጥ አገልግሎቱ እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ስለሺ አመልክተዋል። ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጀምሮ በየደረጃው ላሉ የጤና ባለሙያዎች በሽታው ሲከሰት ምልክቶችን ዓይቶ መለየት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነው። በበሽታው ዙሪያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተካሄዱ ነው ። በቅዱስ ጵውሎስ ሆስፒታል የሥነ አዕምሮ ሐኪም ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ በበኩላቸው በአእምሮ ህመም ምክንያት ከሚከሰቱት ውስጥ እራስን ማጥፋት አደገኛና የዓለማችን ስጋት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። በዓለም ላይ በየዓመቱ 800 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች እራሳቸውን እንደሚያጠፉ በቅርቡ በተካሄዱ ጥናቶች መረጋገጡን አመላክተዋል። "በሀገራችንም ከ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ 7 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት እራሳቸውን ያጠፋሉ" ብለዋል። ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም፣ የገንዘብ እጥረት እና ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ድብርት ለከባድ የአእምሮ ህመም መጋለጥ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ። "ህክምና በመከታተል ከችግሮቹ በቀላሉ መላቀቅ ይቻላል" ያሉት ዶክተር ሙሉቀን ለችግሮቹ ላለመጋለጥም መንፈሳዊ መንገድን መከተል፣ከቤተሰብና ከማህበረሰብ ድጋፍ ማግኘት መፍትሄ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ከመገናኛ ብዙሀንና ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የዘንድሮው የዓለም ጤና ቀን የተከበረው “የአእምሮ ጤናን ማጎልበትና ራስን የማጥፋት ችግርን መከላከል”  በሚል ሀሳብ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም