መወነጃጀል መገለጫው የሆነው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መጓተት

93
አየለ ያረጋል (ኢዜአ) መቼስ ለዕለታዊ ጉርሳችን መሙላት ሰርክ መዘዋወር ግድ አይደል! እናም በዝውውር መንገዳችን ላይ (...) ዕልፍ ትዕይንቶችን ያጋጥማሉ። "ጎዳናው ጎዳናው ጎዳናው መንገድ፤ አንድም የሚጠላ ያመጣል አንድ የሚወደድ" እንዲል ዘፋኙ የጎዳና ላይ ገጠመኞች የተለያዩ ናቸው፤ አንድም የምንወደው ሁለትም የምንጠላው። ወሬ አይደበቅምና በውስብስቡ አዲስ አበባ በመንገዳችን ላይ ገጠመኛችን ብቻ አይደለም፤ ራሱ የሚጠላ የሚወደድ ገጽታዎች አሉት። ውስብስብ ትራንስፖርት ለሰዓታት ተሰልፈን እንሳፈራለን፤ እስከ መዳረሻችን የጎዳናው ነገር ሌላ ዓቢይ ጉዳይ ነው። ይዘጋል፣ ይጠባል፤ ይሰፋል፤ ይፈርሳል። በዚህ ዑደት የመንገድ ግንባታ ሁኔታ ለዓመታት ይጓተታል። ግንባታቸው የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ እልፍ እንግልት ማስከተላቸውን ቀጥለዋል። ይህም ለነዋሪዎቿ ምሬት ብቻ አላተረፈም፤ ለከተማዋ ገጽታ መጉደፍ፤ ለመንግስት ወጪ መናር ጭምር እንጂ። አብዛኛው ህብረተሰብ እግረኛ በመሆኑም ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። ለመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት ዋናው መንስዔ የወሰን ማስከበር ችግር እንደሆነ ሁሌም የሚነገር ትርክት ነው። ከሰሞኑ "የመንገድ መሰረተ ልማትና የወሰን ማስከበር ተግዳሮቶችና የባለደርሻ አካላት ሚና" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፌ ነበር። በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት የዘርፉን ችግር በዝርዝር አንስተዋል። አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ርዕሰ መዲናነት አልፋ፣ ለአፍሪካ ህብረትና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ ሶስተኛዋ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል ናት። በሌላ በአገር ውስጥ የሚደረገው ፍልሰት የመዲናዋ ነዋሪዎችን አሀዝ በፍጥነት እያሻቀበው መሆኑ ይታወቃል። ይህ ወደመዲናዋ የሚደረግ ፍልሰት የከተማዋን ሁለንተናዊ ኑባሬ አቃውሶታል። በተለይም አሁን ላይ አብዛኞቹ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ከመሃል ከተማ ወደ ዳር አዙረዋል። ከዚህም አልፎ ወደ አጎራባች ከተሞች የሚኖሩ አዲስ አበቤዎች ተበራክተዋል ይላሉ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኘ። በዚህም የትራንስፖርቱ እንቅስቃሴ ተወሳስቧል፤ ውስብስቡ የትራንስፖት ስርዓት የመንገድ መሰረተ ልማት ፍላጎቱን አንሮታል። ስለሆነም በአንድ በኩል ለአገር ገጽታ፤ በሌላ በኩል ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ የመንገድ መሰረተ ልማት መዘርጋት ግዴታ እንደሆነ ኢንጂነር ሃብታሙ ይናገራሉ። በዚህም ከተማ አስተዳደሩ እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 300 ኪሎ ሜትር መንገድ ለማሰራት ከ40 እሰከ 50 ቢሊዮን ብር የተገመተ በጀት መታቀዱን አብራርተዋል። ነገር ግን የመንገድ መሰረተ ልማት ጉዳይ አሁን ባለው አኳኋን መቀጠል እንደሌለበት ይስማማሉ። በዕለቱ እንኳን በወሰን ማስከበር መንስኤነት ግንባታቸው መጠናቀቅ ከነበረበት እስከ 5 ዓመታት የዘገዩ 39 የመንገድ ፕሮጀክቶች ለአብነት ተነስተዋል። ከነዚህ መካከል በክፍለ ከተማ ሲተነተኑ በአራዳ 3፣ በየካ 3፣ በቦሌ 3፣ በቂርቆስ 5፣ በጉለሌ 7፣ በልደታ 1፣ በአዲስ ከተማ 1፣ በኮልፌ ቀራኒዮ 8፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ 2፣ በአቃቂ 6 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። የወሰን ማስከበር ስራዎች በተለይም ከፕላን ውጭ የተሰሩ ህንጻዎችና ታላላቅ የመሰረተ ልማቶች መስመሮች ሲያጋጥሙ በዲዛይን ወቅት የሚኖረው ውሳኔ፤ የአዲስ አበባ ቤቶች ፕሮጀክት በተለያዩ ስፍራዎች(ለምሳሌ  በቦሌ አራብሳ፣ በቱሉ ድምቱ፣ በካራ ቆሬ፣ በሰንጋ ተራ፣ በቅሊንጦ፣ በአያት) የሚያስገነባቸው መንገዶች እንዲሁም በኮንትራት የሚገነቡ የማስተር ፕላን ፕሮጀክቶች በስፋት እንደማይሰሩ ተገልጿል። በነዚህ ምክንያቶች ፕሮጀክቶቹ በእጅጉ ስለሚጓተቱ ህብረተሰቡን ለእንግልት፣ መንግስትን ለአማካሪ መሀንዲሶች ክፍያን ጨምሮ ለተጨማሪ በጀት በማስወጣት ለሀብት ብክነት፣ ለመንገዶች በታቀደላቸው ፍጥነትና ጥራት አለመጠናቀቅና ሌሎች መዘዞችን እያስከተሉ ይገኛሉ። እግረኛንና ተሽከርካሪን ለጉዳት ከማጋለጣቸው በተጨማሪ ለከተማዋ ገጽታ መጉደፍ ይተርፋሉ። የወሰን ማስከበር ሲባል ከግለሰብ  ቤቶች ባሻገር በመንግስት የመሰረተ ልማት አቅራቢ (ቴሌ፣ ውሃና ፍሳሽ፣ መብራት) ድርጅቶች ንብረቶች ጉዳይ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በከተማ መልሶ ማልማት ሂደት በታቀደለት ጊዜ አለመጠናቀቅና በፍርድ ቤት ዕግድ የተጣለባቸው ቤቶችም ሌላው ለፕሮጀክቶች ለዓመታት መጓተት መንስኤ ሆኗል። በህብረተሰቡ በኩልም በተጠየቀው ልክ ፈጥኖ ቤቶችን አለማፍረስ፣ ማስተር ፕላኑን ባለመረዳት እንዲያፈርስ ሲጠየቅ የሌላው ግለሰብ ግራቀኝ ለምን አይፈርስም የማለት፤ ከፕላን ውጭ አስጠግቶ የማጠርና አላስፈላጊ የፍርድ ቤት ክርክር እንደሚስተዋሉ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የምህንድስና ዘርፍ ምክትል ሃላፊው ኢንጂነር አብርሃም ኤፍሬም ያብራራሉ። የመሰረተ ልማት አቅራቢዎችን፣ መሪ ፕላን ኮሚሽን፣ ክፍለ ከተሞች፣ መሬት አስተዳድር፣ አማካሪና ስራ ተቋራጮችና መንገዶች ባለስልጣን የወሰን ማስከበር ስራ ባለድርሻዎች መሆናቸውን የሚገልጹት ኢንጂነሩ፤ 'ተቋማቱ ሚናቸውን ተቀናጅተው በአግባቡ ባለመወጣታቸው ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ነው' ባይ ናቸውል። ክፍለ ከተሞች ቤቶችን በጊዜና በተፈለገው መጠን ያለማንሳትና የመንገድ ፕሮጀክቶችን በዕቅዳቸው ያለማካተት ችግሮች አሉባቸው። የመሰረተ ልማት አቅራቢዎች የዘረጉትን መሰረተ ልማት (ለምሳሌ የመብራት ምሰሶዎች፣ የቴሌ ገመድ፣ የውሃ ቱቦ) የማስነሻ ግምት ቶሎ አለመላክ፣ ንብረቶችን በፍጥነት አለማንሳት፣ የሰው ሃይልና የማቴሪያል ችግሮችን በማንሳት ምክንያት መደርደር፣ ከመሬት በታች ያሉ ንብረቶችን በትክክል አለመለየትና በግንባታ ወቅት ለማንሳት ምላሽ አለመስጠትና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉ ይናገራሉ። በነዚህና ሌሎች ምክንያቶች በሚፈጠር የወሰን ማስከበር ችግሮች በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ለዓመታት ዘርፈ ብዙ ማነቆዎችን ደቅነው ቀጥለዋል። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል በ2005 ዓ ም በዕቅድ የተያዘው የኮካ ኮላ- ጌጃ ሰፈር የ400 ሜትር ፕሮጀክት አንዱ ነው፤ ነገር ግን መንገዱ በቤቶች የተሸፈነ በመሆኑና የወሰን ማስከበር ስራው ባለመጠናቀቁ እስካሁን ወደ ስራ አልገባም። በ2006 ዓ ም የፕሮጀክት ርክክብ የተደረገበት ከአያት አደባባይ-ሰንሻይን ኮንዶሚኒየም- ጎሮ- አራብሳ ኮንዶሚኒየም መንገድ 'አንድ ቤት የመብራት ፖልና ትራንስፎርመር የፍርድ ቤት ዕግድ አለው' በሚል ለረጅም ጊዜ ቆሟል። ከ2006 ዓ ም የፕሮጀክት ርክክብ የተፈጸመባቸው ከፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነ ምህረት-ፈረንሳይ አቦ፣ ዳያስፖራ ታክሲ ተርሚናል፤ የረረ በር- መብራት ሃይል፣ ከ5 ኪሎ-አንበሳ ግቢ-ጃንሜዳ፣ ከወሎ ሰፈር ከሴኔጋል ኤምባሲ-አጎና ሲኒማ፣ ከአፍሪካ ህብረት-ቡልጋሪያ፣ ቀጨኔ- ቁስቋም መንገድ፣ ሽሮ ሜዳ-ሀመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት በመብራትና ቴሌ ፖሎች አለመነሳት ዘግይተዋል። ከኮተቤ- ሩት ትምህርት ቤት፣ ከስፖርት ኮሚሽን- ኮከብ ህንጻ፣ ከወሎ ሰፈር- አትላስ፣ ከቡልጋሪያ ማዞሪያ- ጋዜቦ አደባባይ-መስቀል ፍላወር፣ ቀራኒዮ- አምቦ መንገድና ሌሎችም በቤቶች ወሰን አለመከበር ችግር ብዙዎቹ እልባት አላገኙም። ከቅሊንጦ ኮንዶሚኒየም-አስፓልት መንገድ፣ ከሸክላ ሰፈር-አዲሱ ሰፈር፣ ከረጲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት-ስልጤ ሰፈር ፕሮጀክቶች በፍርድ ቤት ዕግድ ከተጓተቱት መካከል ሲሆኑ ከገነት መናፈሻ-ኮነዶሚኒየም፣ ቱሉ ድምቱ ኮንዶሚኒየም፣ ዘነበ ወርቅ አደባባይ- የቀድሞ ሬዲዮ ጣቢያ፣ አውጉስታ ሬንጅ ማቅለጫ አካባቢ የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በውሃ መስመርና በተያያዥ ችግሮች ፕሮጀክቶቹ ተጓትተዋል። ከነዚህ በተጨማሪ በቅርስነት፣ በእግረኛ መንገድ አለመጠናቀቅና አጥሮች ሳቢያ የተጓተቱም አሉ። ከላይ መረዳት እንደሚቻለው በተለይ የመብራት፣ የቴሌና ውሃና ፍሳሽ ሳቢያ የሚከሰቱ ወሰኖች ችግር ጎልቶ ይስተዋላል። ኢንጂነር ሀብታሙ እንደሚሉትም እያንዳንዱ መሰረተ ልማት አቅራቢ የራሱን አገልግሎት ለመዘርጋት እንጂ ተናቦና ሁሉንም አገልግሎት አቀናጅቶ ለመስራት አይሞከርም። እናም ችግሩ መንግስታዊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ፣ ተጠያቂነት አሰራር የሚሻና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። እነዚህ መሰረተ ልማት አቅራቢዎችም 'ህዝቡ እርካታ የሚያገኘው መንገድን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አገልግሎት በአንድነት መዘርጋት ሲቻል ነው' ይላሉ። ለመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት የሚሆኑ የወሰን ማስከበር ስራዎች በፍጥነት እንዴት አይከናወኑም? ለሚለውም የራሳቸው ምላሽ አላቸው። የኢትዮ ቴሌኮም ተወካዩ አቶ ታከለ መንገሻ እንደሚሉት የመንገድ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ሲሰራ ለኔትወርክ ገመዶች ዝርጋታ የሚውል በቂ ቦታ እንደማይኖር ይገልጻሉ። ነባሩን የኔትወርክ ገመድ (ኬብል) ለመዘርጋት ክፍት ቦታ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፤ ይህ ቦታው እስኪገኝ መስመሮችን ማንሳት ስለማይቻል የወሰን ማስከበር ስራውን በፍጥነት ማከናወን ከባድ መሆኑን ይጠቅሳሉ። አገልግሎቱን በፍጥነት መዘርጋት ካልተቻለ ደግሞ ባንኮችን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ዕለታዊ ስራዎች ስለሚስተጓጎሉ አስቸጋሪ መሆኑን ነው የሚናገሩት። በሌላ በኩል የመንገድ ግንባታ ወቅት ከመንገዱ ግራ ቀኝ ያሉ የኔትወርክ ሳጥኖች መንገዶች ተቆርጠው በመሬት ስር እንደሚቀበሩ ገልጸው፤ ነገር ግን መንገዶች በፍጥነት ባለመገንባታቸው በፍጥነት ሳጥኖችን ማገናኘት እንደማይቻል፤ በዚህ ገመዶቹ እንደሚቆራረጡና ለዘረፋ እየተጋለጡ መሆኑን ያነሳሉ። ስለሆነም የመንገድ ማስተር ፕላን ሲነደፍ የቴሌኮም አገልግሎት ቦታም ሊኖር እንደሚገባና የመንገድ ግንባታዎችም የቴሌን አገልግሎት በማያስተጓጉል ሁኔታ በፍጥነት መካሄድ እንዳለባቸው አብራርተዋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የወከሉት በድርጅቱ የዋየር ቢዝነስ ሃላፊ አቶ ገመቹ ይመር ድርጅቱ ካለበት የሀብት ውስንነት በተጨማሪ የወሰን ማስከበር ጉዳዮችን በፍጥነት ለመከናወን የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲሰሩ የፖል መትከያ ቦታ እንደማይኖር ይገልጻሉ። የኤሌክትሪክ መስመር ለማዛወር ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ የሚገልጹት አቶ ገመቹ፤ ግብዓቶች እስኪገቡ ህብረተሰቡን የሚያማርር ኤሌክትሪክ መቆራረጥ ደግሞ ሌላው አስቸጋሪ ነገር እንደሆነ ያብራራሉ። ይህም የመብራት ፖልና ትራንስፎርመሮችን በአፋጣኝ ለማንሳት ባለመቻሉ የወሰን ማስከበር ችግር እንደሚኖር ጠቁመዋል። ተቋሙ እጅግ በርካታ አገራዊ ተግባራት እንዳሉበት ገልጸው፤ ይህን ተግባሩን ለማከናወን የሰው ሃይልና የሀብት ውስንነስ እንዳለበትም ይናገራሉ። የመንገዶች ማስተር ፕላን ሲሰራ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ቦታ ሊታሰብበት እንደሚገባ የአቶ ታከለን ሃሳብ ይጋራሉ። ለነዚህ መሰረተ ልማት (ለፖል መትከያ) የሚሆን በቂ ስፍራ ባለመኖሩ ሰራተኞቹ ከግለሰቦች ጋር ግጭት ውስጥ እንደሚገቡና ለጉዳት እንደሚዳረጉ ይናገራሉ። በሌላ በኩል መንገዶች ባለስልጣን ለሚያነሳው ንብረት ፈጥኖ ክፍያ እንደማይፈጽም ይናገራሉ። በዚህ በኩል ግን ኢንጂነር ሀብታሙ አይስማሙም። “እንደውም ለስንት ጊዜ የተጠራቀመ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አልከፈላችሁንም” በማለት ይህን አስተያይት አልተቀበሉም። በአራዳ ክፍለ ከተማ  የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤትን ወክለው የተገኙት አቶ እንዳልክ ነጋሽ ችምችም ያሉ ሰፈሮችን ለማፍረስ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በፍጥነት ወሰን እንደማያስከብር ይናገራሉ። ለቀበሌ ነዋሪዎች ምትክ ይሰጣል፤ ለግል ግን ቶሎ ምትክ ቦታ አይሰጥም፤ በተመሳሳይ የዲዛይን ለውጥ ሲደረግ ለቀበሌ ምትክ ይሰጣል፤ ለግል ግን ምትክ አይሰጥም፤ ይህም ማህበረሰቡን እያማረረ ነው ይላሉ። እናም ያለቀለት ዲዛይን መምጣት መተግበር እንዳለበት ነው የሚገልጹት። በሌላ በኩል የፍትህ ተቋማት በዕግድ ዙሪያ ሊተባበሩ እንደሚገባ ይገልጻሉ። አግባብነት የሌላቸው በርካታ የክርክር ጉዳዮች የመንግድ ፕሮጀክቱን ለዓመታት መጓተት መንስኤ እንደሆኑ ገልጸዋል። 'አሁን ላይ እንደውም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ፕሮጀክት የማስተጓጎል ተግባር እየተለመደ ነው' የሚሉት አቶ እንዳልካቸው፤ ፍርድ ቤቶች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ቢተባበር ለአገራዊ መሰረተ ልማት ዝርጋታው ወሳኝ እንደሆነ አስተያየት አላቸው። የፍርድ ዕግድን በተመለከተ አስተያይት የሰጡት በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሬጅስትራር ወይዘሮ ወጋየሁ ሰለሞን መንገዶች ባለስልጣን ችግሩ የሚከሰተው በማህበረሰቡ ዘንድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ባለመፍጠሩ እንደሆነ ያምናሉ። በሕብረተሰቡ ዘንድ በቂ የስነ ልቦና ስራ ተሰርቶ ተመጣጣኝና አስፈላጊው ምትክ በወቅቱ ከተላለፈ ህዝቡ ወደ ሌላ አተካራ እንደማያመራ ይናገራሉ። ነገር ግን በቂ ቅድመ ዝግጅት ሳይኖር ቤቶችን ድንገት እንዲያፈርሱ ሲጠየቅ ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደሚወስደው ይገልጻሉ። ፍርድ ቤት ደግሞ ‘ተበድያለሁ፤ ፍትሕ እሻለሁ፤ ተጠቃሚው እኔ ነኝ’ የሚል አካልን የፍትሕ ስራውን መስራት አለበት። ተወደደም ተጠላም ክርክር ሲጀመር ጉዳዩ እስኪቋጭ ድረስ ማንም ይሁን ማን ጉዳዩ ይታገዳል፤ ክርክሩ እስኪያበቃ ድረስ ዕግዱ ይቀጥላል” በማለት ያብራራሉ። በሌላ በኩል የወሰን ማስከበር ስራው መቶ በመቶ ተጠናቆ ግንባታው መጀመር አለበትም የሚሉ ወገኖች ነበሩ። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ስራዎች ሲጀመሩ 80 በመቶ ስራው ተጠናቆ ነው የሚል አሰራር ተቀምጧል። ይሁንና በዚህ ረገድ ኢንጂነር ሃብታሙ “መቶ በመቶ ቀርቶ 80 በመቶ እንኳን አጠናቆ ለመጀመር አሰራሩ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ወሰን ማስከበር ለማጠናቀቅ ሲባል ትልቅ የትራንስፖርት ቀውስ ለተፈጠረበት ከተማ መሰረተ ልማት በተፈለገው ፍጥነት መዘርጋት አይቻልም” ይላሉ። ስለሆነም ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ግንባታውን ጀምሮ ጎን ለጎን ቀሪ የወሰን ማስከበር ተግባራትን ማከናወን እንደሚቀል ነው የሚናገሩት። ሁሉም ተቋማት እንደ መፍትሔ የሚስማሙበት ነገርም አለ፤ የወሰን ማስከበር ጉዳዮችን የሚከታተል በየተቋማቸው አንድ ኮሚቴ በማዋቀር ሂደቱን በፍጥነት መከታተል የሚል። በዚህ ዘርፍ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ባለፈው ዓመት የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ፕሮግራም ማስተባባሪያ ኤጄንሲ የሚል ተቋም መመስረቱ ይታወሳል። በኤጀንሲው የግንባታ ፈቃድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረመድህን እንዳሉት ድርጅቱ ራሱን ሲያደራጅ ቆይቷል። በዚህም እስካሁን የሚጨበጥ ስራ አለመስራቱን ይገልጻሉ። በቀጣይ ዓመት ግን ኤጀንሲው ወደ ሙሉ ተግባሩ እንደሚገባ አብራርተዋል። በተለይም የወሰን ማስከበር ችግሩ ይበልጥ በሚስተዋልባት አዲስ አበባ በከተማ ደረጃ አንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ራሱን እያደራጀ መሆኑንም ገለጸዋል። ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ውሃና ፍሳሽና መንገዶች ባለስልጣን መሰረተ ልማት ሲዘረጉ የጋራ ዕቅድ እንዲያወጡ ማድረግ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባያስወግድም ማቃለል እንደሚቻል አቶ ሰለሞን ይናገራሉ። የወደፊት አሰራሩም ይህን ስርዓት መዘርጋት እንደሆነ አረጋግጠዋል። “የመሰረተ ልማት ችግሮች የሚፈቱት የመጀመሪያው ነገር መረጃ ይዞ ዕቅድ ላይ በጋራ መግባት ነው። ዲዛይን ላይ አንድ ላይ መሰራት አለበት። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። አሁን ላይ ግን መሰረተ ልማቶች ቀደም ብለው በተለያየ መንገድ የተጀመሩ ናቸው” በማለት ችግሩን ይገልጻሉ። ወደፊት በአዲስ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ግን የመሰረተ ልማት አገልግሎት አቅርራቢዎች (ቴሌ፣ መንገድ፣ መብራትና ውሃና ፍሳሽ) ዘላቂው መፍትሔ በዲዛይን ጊዜ አንድ ላይ እንዲገቡ ማድረግ መሆኑን ገለጸዋል። በዚህም የወሰን ማስከበር ችግር ለተተበተበው የመንገድ መሰረተ ልማት የተሻለ ተስፋ ይኖራል የሚል እምነት አላቸው። የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሲጓተት እከሌ ይህን ስላላደረገ ነው፤ እከሌ እንዲህ ስላልሆነ ነው፣ እከሌ ምላሽ ስላልሰጠኝ ነው፤ በማለትና በመወነጃጀል ሰበብ ማቅረቡ እልባት ማግኘት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም