የሰላም ጉዳይ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ ለመስራት መዘጋጀቱን የሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ

61
አዲስ አበባ መስከረም ኢዜአ መስከረም 30 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን የአገራዊ ሰላም ጉዳይ ዋነኛው የትኩረቱ አርጎ ለመስራት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ የ2011 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸምና በ2012 ለማከናወን በታሰቡ እቅዶች ዙሪያ ውይይት አድርጓል። የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ገነት ስዩም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በቀጣይ የአገር ሰላም ጉዳይ አይነተኛ የትኩረት አቅጣጫ በማድርግ ለመስራት ታቅዷል። ቀደም ሲልም በሰላም ጉዳይ የተከናወኑ ስራዎች ቢኖሩም አጥጋቢ አልነበሩም ያሉት ዳይሬክተሯ በቀጣይ ለማጠናከር መታቀዱን ተናግረዋል። በአገሪቷ ችግሮች ሲፈጠሩ ይፈቱባቸው የነበሩ ባህላዊ እሴቶችን መልሶ በመገንባት ግጭቶች ሳይከሰቱ ለመፍታት እንዲያስችል አገር አቀፍ የሴቶች ምክረቤት ለማቋቋም መታቀዱንም ገልጸዋል። የኦሮሚያ የሴቶች ፌዴሬሽን ምክርቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ እንዳሉት ሴቶች ለአገር ሰላም የመፍትሄ አካል በመሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአቶችን መልሶ በመገንባት ሂደት ሴቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። የአማራ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ እመቤት ምትኩ እንዳሉትም መልካም የሆኑ እሴቶችን በማስተዋወቅና በማስተማር  አገር ወዳድ ዜጋ መፍጠር የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል። በተለይ ሴቶች ከቤተሰብ ጀምሮ ለአገር መልካም አርአያ የሚሆን ዜጋ ለማፍራት በማነፅና በማስተማር ለሰላምና አብሮነት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ግጭቶች ሲከሰቱ በማርገብ ሰላምን ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ በመስራት የሁሉም ዜጋ ድርሻ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል። የፌዴሬሽኑ አባላት በአገሪቷ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መንግስት በመከላከል ላይ አተኩሮ እንዲሰራም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም