ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ያደረገልን አቀባበል ትምህርታችንን በንቃት ለመጀመር አነሳስቶናል- አዲስ ገቢ ተማሪዎች

84
ሆሳእና መስከረም 30/ 2011- የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ያደረገልን ቤተሰባዊ አቀባበል ትምህርታችንን በንቃት ለመጀመር አነሳስቶናል ሲሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለፁ። ዩኒቨርሲቲው ከትናንት በስተያ ጀምሮ ለተመደቡለት አዲስ ተማሪዎች አቀባበል እያደረገ ነው። ከደቡብ ጎንደር ዞን ሀንዳቢት ወረዳ ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጣችው ተማሪ ማህሪት ጉሊት ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት ምደባዋን ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በምን መልኩ እንደምትቀላቀል ስታስብ ቆይታለች ። "የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ  አባላት ከሆሳእና መናኽርያ ጀምሮ ያደረጉልኝ ቤተሰባዊ አቀባበል ግን ሀሳቤን አቅልሎልኛል" ብላለች ። ከመናኽሪያ በተደረገላት አቀባበል በቀላሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመድረስ ምዝገባዋን አጠናቃ መኝታ ቤት መረከብዋን  ተናግራለች ። "ከምኖርበት አካባቢ ስወጣ የመጀመርያዬ በመሆኑ ጭንቀት ተሰምቶኝ ነበር" ያለው ደግሞ ከአርሲ ዞን ሸርካ ወረዳ የመጣው ተማሪ ብሩክ ኃይሉ ነው። "ሆሳእና መናኽርያ እንደደረስኩ የዩኒቨርሲቲውን መለያ ያደረጉ ሰዎች ተቀብለውኝ ወደ ግቢው ሲወስዱኝ ከጭንቀቴ ተላቀኩ " ብሏል ። "በዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ እንደነበር አስቀድሞ መረጃው ነበረኝ" ያለው ተማሪ ብሩክ የተደረገለት አቀባበል በዩኒቨርሲቲው መመደቡን ሲያውቅ ተሰምቶት የነበረውን ደስታ የበለጠ ያጠናከረው መሆኑን ገልፅዋል ። ከጊቢው ተማሪዎች ጋር አብሮነትን በማጠናከር የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት በትጋት እንደሚሰራ ተናግሯል ። ከአዲስ አበባ ወደ ዩኒቨርሲቲው ልጃቸውን ይዘው የመጡት አቶ ሰላሙ ካልቲሶ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ትራንስፖርት በመመደብ ከመናኽርያ ጀምሮ ያደረገላቸው አቀባበል አስደሳች እንደነበር ገልጸዋል ። ዩኒቨርሲቲው የመደባቸው አካላት የነበራቸው የመረጃ አሰጣጥና ቅንጅታዊ መስተንግዶ  አዲስ ተማሪዎችን ያለ ስጋት ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል ። ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ትምህርታቸውን በትጋት ሊከታተሉ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል ። የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በተማሪዎች  አቀባበል ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ቀድሞ የነበረው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ። ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ለትምህርታቸው ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ መክረዋል ። ዩኒቨርስቲው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር  በተሰጠው መመሪያና በተማሪዎች ስነ ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት እንደሚሰጥ ተናግረዋል ። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ ለመቀጠል አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ። ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን 3ሺህ 900 አዲስ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ታውቋል ።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም