የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን የደስታ መልዕክት አስተላለፉ

191
አሶሳ /ሀረር ኢዜአ መስከረም 30 / 2012  የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰጠውን የሰላም ኖቬል ሽልማት በማስመልከት የደስታ መልዕክት አስተላለፉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያገኙት ዓለም አቀፍ የሰላም ኖቬል ሽልማት በቀጣይም ሃገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የማድረስ የአመራር አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ተናገሩ፡፡ ርዕሰ መስተዳሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሽልማት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ሀገርንም የሚያኮራ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ስኬት ለሽልማት መብቃታቸው ለሌሎች አመራሮችና ለህብረሰቡም የአሸናፊነት ስሜት ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም እድል ከተሰጣቸው ሠላም በማስፈን ጥረታቸው ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ፖለቲካና  ኢኮኖሚ እድገት ወደ ተሻለ ማድረስ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በግላቸው ሽልማቱን ሲሰሙ በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደስታ መልዕክት አስተላለፈ፡፡ ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ ሽልማቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም፣ የይቅርታና የእርቅ ሰላም ስራ ፍሬ ነው ያለው መግለጫው ሽልማቱ  የመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ሽልማት ጭምር በመሆኑ እንኳን ደስ ያለን መልእክት አስተላልፏል። በሽልማቱ የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት የተሰማውን ደስታና ኩራት ይገልፃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም