የፍጆታ ምርቶች ለተጠቃሚው በትክክል እንዲደርሱ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

75
ባህርዳር ሰኔ 9/2010 መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸው የፍጆታ ምርቶች ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በትክክል እንዲደርሱ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የንግድ ሚኒስቴር አሳሰበ። በመሰረታዊ ምርቶች አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል በሚቻልበት ላይ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሄዷል። የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት እንደሀገር በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የተስተዋለውን እጥረት ለማስተካከል መንግስት በድጎማ ለህብረተሰቡ ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ እያቀረበ ይገኛል። በየወሩም ዘይት ከ40 ሚሊዮን ሊትር በላይ፣ ስኳርና ለዳቦ ዱቄት የሚሆን ስንዴ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን 200 ሺህ ኩንታል በላይ በድጎማ ለህብረተሰቡ በማቅረብ እያሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸው መሰረታዊ ምርቶች በራሱ መዋቅርና እንዲያከፋፍሉ ባስቀመጣቸው አደረጃጀቶች ለተጠቃሚው በትክክል እየደረሱ ባለመሆኑ የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መጥቷል። ለዚህ ዋነኛው ችግር ደግሞ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም በመሆኑም በቀጣይ መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል። አሁን እየቀረበ ያለውም ቢሆን ለህብረተሰቡ በትክክል እየደረሰ ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት ራሳቸውን ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በማራቅ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል። የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ  በበኩላቸው  መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ለክራይ ሰብሳቢነት እየተጋለጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል። "በድጎማ የሚቀርቡ ምርቶች በትክክል ለተጠቃሚው ባለመድረሳቸውም ህብረተሰቡ መብትና ጥቅሙን እንዲያጣ አድርጎታል" ብለዋል። በተያዘው ዓመት በድጎማ ለህብረተሰቡ ከቀረበው ውስጥ አንድ ሺህ 453 ኩንታል ስኳርና የዳቦ ዱቄት፣ ከ131 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይትና 25 ሺህ 598 ሊትር ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ መያዙን  በመጥቀስ ችግሩን አመላክተዋል። ከተያዘው ምርትም ውስጥ  በፍርድ ውሳኔ ተመልሶ ለተጠቃሚው ቀርቦ እንዲሰራጭ እየተደረገ እንዳለም ተናገረዋል። ክልሉ ከፌዴራል መንግስት በድጎማ በየወሩ 145 ሺህ 734 ኩንታል ስኳርና ያልተፈጨ ስንዴ፣ እንዲሁም ከሰባት ሚሊዮን 762 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እየቀረበለት እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። አሁን እየቀረቡ ያሉት የፍጆታ ምርቶችም ለክልሉ አጠቃላይ ከሚያስፈልገው ከ26 እስከ 36 ነጥብ አራት በመቶ እንደማይበልጥም ነው አቶ ተዋቸው ያስረዱት። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ቡሬ የሚገኘው የዳሞት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው እሸቱ በበኩላቸው መንግስት ለህብረተሰቡ እንዲያከፋፍሉ በድጎማ የሚያቀርብለትን ምርቶች ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እያከፋፈሉ መሆናቸውን  አስረድተዋል። "ይህም ሆኖ በጥቁር ገበያ አንድ ኪሎ ስኳር እስከ 100 ብር ለህብረተሰቡ በድብቅ እየተሸጠ በመሆኑ ቢሮው ህግና ስርዓት እንዲይዝ መስራት ይኖርበታል" ብለዋል። የዳቦ ዱቄትን በጥራት አዘጋጅቶ ለተጠቃሚው ለማድረስ 30 የዱቄት ፋብሪካዎች ባለፉት አምስት ወራት ማህበር መስርተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል የዱቄት አምራቾች ዘርፍ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ብርቁ መለሰ ናቸው። አቶ ብርቁ እንዳሉት ፋብሪካዎቹ በዋናነት የጋራ ማህበር መስርተው ለመንቀሳቀስ የወሰኑት መንግስት በድጎማ የሚያቀርበውን ስንዴ በጥራት ፈጭቶ ለዳቦ ቤቶችና ለአከፋፋዮች በማቅረብ ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ለማስቻል ነው። የስኳር ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በዛብህ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው የስኳር አቅርቦት እጥረት እያጋጠመ ያለው በግንባታ ላይ የሚገኙ 10 ፋብሪካዎች ተጠናቀው ምርት ባለመጀመራቸው መሆኑን ገልጸዋል። ከነዚህ መካከል ማምረት የጀመሩትን የተንዳሆ፣ የከሰም፣ የኩራዝና የአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካዎችን በመጪው ዓመት በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ እጥረቱን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ቢሮው ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የንግድ ሚኒስቴር፣ የስኳር ኮርፖሬሽንና የእህል ንግድ ድርጅትን ጨምሮ ከክልሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም