አንድነት ፓርክ መላ አፍሪካን ማስተሳስር የሚችል ታሪካዊ ስፍራ ነው---በአዲስ አበባ የሚኖሩ ዲፕሎማቶች

85
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 30/2012 አንድነት ፓርክ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንንም የሚያስተሳስር ታሪካዊ ስፍራ መሆኑን በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው ዲፕሎማቶች ተናገሩ። በታላቁ ቤተ መንግስት የተገነባው አንድነት ፓርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ በኢጋድ አገራት መሪዎች ትናንት ተመርቆ ሲከፈት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችም ስነ ስርዓቱን ታድመዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው ዲፕሎማቶች ፓርኩ የተደራጀበት መንገድ እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል። በፓርኩ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችም ከኢትዮጵያጵያ ባለፈ የአፍሪካዊያን ነጸብራቆች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት። በአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ ተወካይ ሌቲ ቺዋራ ፓርኩ ኢትዮያውያን ታሪካቸውን እንዲያውቁና የራሳቸው እንዲያደረጉ ያስችላል ብለዋል። ቤተ መንግስቱ ለጉብኝት ክፍት መሆን ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ የማድረጉን ኃላፊነት አጠናክራ መቀጠሏን እንደሚያሳይ ተናግረዋል። ፓርኩን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች እግረ መንገዳቸውን የአፍሪካ ህብረት ምን እንደሆነና የት እንደተወለደ በቀላሉ መረዳት ይችላሉ ብለዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን በበኩላቸው አፍሪካን የሚወክሉ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መጥፋታቸውን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን ጠብቀው በዚህ መልኩ ሰንደው ለእይታ ክፍት ማድረጋቸው የሚያስደንቅ መሆነንም ገልጸዋል። "የፓርኩ ለህዝብ ክፍት መሆን ለዜጎች ቅድሚያ የሚሰጥና ትልቅ አገር ለመገንባት ቁርጠኛ የሆነ መንግስት መኖሩን ያሳያል" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬነር ናቸው። ቤተ መንግስቱ ለህዝብ ክፍት መሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከጀመረው ሪፎርም ጋር የሚያያዝ  መሆኑንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም