ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል አደረገላቸው

72
አዲስ አበባ መስከረም 30 /2012 በአካባቢው ማህበረተሰብ የተደረገልን አቀባበል የህዝቡ ፍፁም ሰላምና ፍቅር ወዳድነት ለማረጋገጥ አስችሎናል ሲሉ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ተማሪዎችና ወላጆች ገለፁ። ተማሪዎቹ በማህበረሰቡ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በአካባቢው ሰላም ላይ ልባዊ መተማመን እንዲያሳድሩና ለትምህርታቸው በተረጋጋ መንፈስ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል ። በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ተማሪዎች ያለምንም እንግልት እንዲገቡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው የተመደበ ልጃቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ይዘው የመጡ ወይዘሮ መቅደስ ጽጌ በሰጡት አስተያየት የአካባቢው ማህበረሰብ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግድበት መንገድ ፍፁም ትህትና የተሞላበት ነው ብለዋል ። ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ከተማ ድረስ ተሽከርካሪዎችን መድቦ በነፃ ማመለለሱ ተማሪዎችን ከወጪ ከማዳኑም በላይ አካባቢውን ለማያውቁ ተማሪዎች ከስጋትና እንግልት መጠበቅ መቻሉን እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል። ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ከአባይ ጮመን ወረዳ የመጡት ወላጅ አቶ ጋሩማ መርጋ በበኩላቸው በአካባቢው ህዝብ የተደረገላቸው አቀባበል አድናቆት እንደጫረባቸው ተናግረዋል ። የአካባቢው ነዋሪዎች በባህላቸው መሰረት ድንኳን ጥለው ያደረጉላቸው መስተንግዶ ልጃቸው ፍፁም ጨዋ ከሆነ ህዝብ ጋር መቀላቀሏ የሚያመላክት በመሆኑ ስለቀጣይ ደህንነቷ እንዳያስቡና እንዳይሰጉ ማፅናኛ እንደሆናቸው ገልፀዋል ። ከአርሲዞንየመጣችውተማሪፀደይዝምበላቸው እንዳለችው ደግሞ የአካባቢውነዋሪናየዩኒቨርሲቲውማህበረሰብያደረገልንመስተንግዶ በቀጣይበሰላምበመማርስኬታማእንድንሆንመነሳሳትይፈጥርልናልብላለች። ከዚሀም ሌላ ተማሪዎች ፍቅርንና አንድነትን ሰንቀን ፣ ከዘረኝነትና ከብጥብጥ እርቀን የአካባቢውን ሰላም ከሀብረተሰቡ ጋር ሆነን ለመጠበቅ የሚያስችል አደራ ጭምር ከህዝቡ ተቀብለናል ስትል ተናግራለች ። በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳሪክቶሬት ዳሪክተር አቶ አህመድ መሀመድ በበኩላቸው በዚህ አመት ወደ ዩኒቨርስቲው 3 ሺህ 600 አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተመድበዋል። ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ በመንገድ ላይ እንግልትና መጉላላት እንዳይደርስባቸው ከአዲስ አበባ ድረስ ተሽከርካሪ በመመደብ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። በደሴ መስመር ለሚመጡ እንግዶች ደግሞ ከደብረብርሃን መናኸርያ በመቀበል የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎትም መሰጠቱን ተናግረዋል። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ሲደርሱ እንዳይደናገሩ ሲባል ቀደም ብሎ የመኝታ ክፍሎች ዝግጅትና ምደባ ተከናውኗል ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ አመት 12 ሺህ የሚደርሱ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራው ለማከናወን መዘጋጀቱን መረጃዎች ያመላክታሉ ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም