የሚገጥሙን እንቅፋቶች ሳይበግሩን ኢትዮጵያን የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን መስራት እንቀጥላለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

69
መስከረም 30/2012 ''የሚገጥሙን ማናቸውም አይነት እንቅፋቶች ሳይበግሩን ኢትዮጵያን የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን መስራት እንቀጥላለን'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድነት ፓርክ መከፈት ቤተ መንግስት በመገዳደልና በኃይል የሚገባበት ቦታ ሳይሆን አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም መሆኑን ልጆቻችን ተረድተው እንዲያድጉ ይረዳል ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በታላቁ ቤተ መንግስት የተገነባው የአንድነት ፓርክ ትናንት በእርሳቸውና በተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች ተመርቆ ለህዝብ ክፍት በሆነበት ወቅት ነው። የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሶቬኒ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትን ጨምሮ የተለያዩ  የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ባለስልጣናት በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ታድመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት የመደመር እሳቤ አገር ወረትም ውዝፍ እዳም አለባት ብሎ እንደሚተነትን አስረድተዋል። በመሆኑም ወረትን ማከማቸት ውዝፍ እዳን ከስር ከስሩ መቀነስ ይገባል ነው ያሉት። ነገር ግን በውዝፍ እዳዋ እያላዘኑ የአገርን ወረት ማሳነስ አይገባም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የስልጣኔ ቁልፉ ትናንትን በመዘከር፣ ዛሬን መኖርና ነገን አሻግሮ መመልከት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። በመሆኑም ቀደምት አባቶች የሰሩት ጀግንነት እንደሚያኮራ ሁሉ ዛሬ ላይ ሆነን ከሰሩት ጥፋት ነገን የሚያሻግር ትምህርት መቅሰም እንደሚገባ መክረዋል። የኢትዮጵያን ብልጽግና መሰረት የምንጥልበት ጊዜ አሁን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስራው ግን አልጋ በአልጋ እንደማይሆን እንደሚረዱ ገልጸዋል። ነገር ግን ያሰብነውን  ከመስራት ፈጽሞ የሚያቆመን የለም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እናሸንፋለን፤ የምናሸንፈው ሰውን ሳይሆን ነገአችንን ነው" ሲሉም ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በረዥሙ ዘመን ታሪካቸው ጥሩም መጥፎም ሁነቶችን ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል። "ታሪክ ታሪክ ሆኖ ይቀጥላል፤ ልንለውጠውም አንችልም" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ካለፈው ነገር  ተምረን ነገን በጋራ መገንባት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ይህን እንደሚያሳይ በመጠቆም።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም